የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የምርጫ አጀንዳዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የምርጫ አጀንዳዎች
46ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ስብሰባው እየተካሄደ የሚገኘው “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
ከህብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት አጀንዳዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛው የምርጫ ጉዳይ ሲሆን ምክር ቤቱ በስብሰባው በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ስር የሚገኙ ስድስት ኮሚሽነሮች ምርጫ ያካሂዳል።
እጩዎቹ ከሚወዳደሩባቸው መካከል የ’ግብርና ገጠር ልማት ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽን፣ የኢኮኖሚ ልማት፣ የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽን፣ የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽን ይገኙበታል፡፡
እንዲሁም እጩዎቹ የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽን፣ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽን እና የጤና፣ ሰብአዊ ጉዳዮችና የማህበራዊ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለመሆን ይወዳደራሉ።
ስድስቱ ኮሚሽነሮች የሚመረጡት ከማዕከላዊ፣ ደቡብና ምዕራብ አፍሪካ ቀጣናዎች ሲሆን የስራ ዘመናቸው አራት ዓመት መሆኑ ተጠቅሷል።
ምክር ቤቱ የአፍሪካ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አባል ለመሆን የአምስት ሀገራት ምርጫም ያካሂዳል።
ኢትዮጵያ ለሶስት ዓመታት (በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2025 እስከ 2027) ድረስ ለሚቆየው የምክር ቤት አባልነት ትወዳደራለች።
በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የዓለም አቀፍ ህግ አማካሪ ቡድን የስድስት አባላት እና የአፍሪካ ህብረት የፀረ-ሙስና አማካሪ ቦርድ የአምስት አባላት ምርጫ ይከናወናል።
የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም ለአፍሪካ ስፔስ ኤጀንሲ እና የአፍሪካ ህብረት የህጻናት መብቶች እና ክብካቤ የባለሙያዎች ኮሚቴ በተመሳሳይ የአንድ አንድ አባላት ምርጫ ይከናወናል።
46ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ እስከ ነገ ይቆያል።
የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር እና ምክትል ሊቀመንበር ምርጫ ይካሄዳል።