ክልሉ የጉባዔውን የትኩረት አቅጣጫዎች ተከትሎ ወደ ትግበራ ገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
ክልሉ የጉባዔውን የትኩረት አቅጣጫዎች ተከትሎ ወደ ትግበራ ገብቷል
አሶሳ፤ የካቲት 5/2017(ኢዜአ)፦ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ የትኩረት አቅጣጫዎች ወደ ትግበራ መግባቱን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ተናገሩ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ብልፅግና ፓርቲ ክልሉን "ከዳር ወደ መሃል" በመውሰድ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ተሳታፊና ውሳኔ ሰጪ እንዲሆን ማድረጉን ጠቁመዋል።
ፓርቲው በጉባዔው የአገሪቷን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት የትውልድ ግንባታ ላይ በትኩረት እንዲሰራም አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።
ማህበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥም የጤና ዘርፉን ማዘመንና የጤና ተቋማት ማሻሻል የክልሉ መንግስት ዋነኛ ትኩረት ናቸው ብለዋል።
የክልሉን ሠላም በማጽናት የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የክልሉ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑንም አቶ ጌታሁን ገልጸዋል።
በክልሉ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ለምቶ የዜጎች የገቢ ምንጭ እንዲሆን እና ለሀገር ኢኮኖሚ የራሱን ድርሻ እንዲያበረክት ክልሉ በልዩ ሁኔታ ተግባራዊ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለክልሉ የተለየ ፀጋ ይዞ መጥቷል ያሉት አቶ ጌታሁን፤ ለአብነትም ወጣቶች በግድቡ በዓሳ ምርት ላይ ውጤታማ ስራ እያከናወኑ መሆኑንም አክለዋል።
የክልሉ ምቹ የግብርና ልማት አቅም በመጠቅም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ገቢን ለማሻሻል ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።
"ፓርቲው በሐሳብ ብቻ የመወዳደር ትግልን እያለመመደ ነው" ያሉት አቶ ጌታሁን፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ኢትዮጵያን አሻጋሪ የሚያደርጉ ሐሳቦችን በማቅረብ በትብብር ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
የፓርቲው ውሳኔዎች የህብረተሰቡን ብልፅግና የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልፀው፤ ይህም የሁሉንም ትጋት እና የመፈጸም አቅም ይጠይቃል ብለዋል።