ቀጥታ፡

የሐጅ ተጓዦች በተቀመጠው ጊዜ ምዝገባቸውን እንዲያከናውኑ ምክር ቤቱ አሳሰበ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 04/2017(ኢዜአ)፦ የዘንድሮ የሐጅ ተጓዦች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ምዝገባቸውን ሊያከናውኑ እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አሳሰበ።

ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም የ1 ሺህ 446 ኛው የሐጅ ጉዞ ምዝገባ በተለያዩ አካባቢዎች ከጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ሃላፊ ሼይኸ አብዱልአዚዝ ሼይኸ አብዱልወሊ የዘንድሮውን የሐጅ ጉዞ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ምክር ቤቱ 1ሺህ 446 ኛው የሐጅ ጉዞ ለማድረግና ለሙስሊሙ ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።

ከዚህም መካከል አንዱ የሐጅ የሚያደርጉ ተጓዦችን መመዝገብ ሲሆን፤ ይህም በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለማከናወን ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቀጣይም የምዝገባ ሂደቱን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለመጨረስ በሐጅ ጉዞ የሚያደርጉ ተጓዦች የመመዝገቢያው ጊዜ ሳይጠናቀቅ ከወዲሁ ሊመዘገቡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለ2017 ዓ.ም የሀጅ ጉዞ 10 ሺህ ሰዎችን ለመመዝገብ እቅድ መያዙ የተገለፀ ሲሆን፤ ምዝገባውም እስከ ረመዳን ድረስ ብቻ የሚቆይ እንደሆነ በማብራሪያው ተጠቅሷል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም