የመከላከያ ሚኒስትሯ ህንድ ባዘጋጀችው Aero India 2025 ላይ እየተሳተፉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሚኒስትሯ ህንድ ባዘጋጀችው Aero India 2025 ላይ እየተሳተፉ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢ/ር አይሻ መሀመድ ህንድ ባዘጋጀችው Aero India 2025 ላይ እየተሳተፉ ነው።
ሚኒስትሯ ባንጋሎር አየር ሃይል ጣቢያ በትናትናው ዕለት በተከፈተው Aero India 2025 ላይ በመካፈል ላይ ሲሆኑ ኤግዚቢሽኑ ህንድ የደረሰችበትን የላቀ ወታደራዊና የሲቪል አቪየሽን ቴክኖሎጂ ያሳየችበት መሆኑም ተገልጿል።
THE RUNWAY TO A BILLION OPPORTUNITIES በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለው Aero India 2025 ህንድ በየሁለት ዓመቱ የምታካሂደው የአየር ትርኢት እና የወታደራዊ አቪዬሽን ኤግዚቢሽን ነው።
ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ የመከላከያ ሚኒስትሮች፣ ወታደራዊ አዛዦችና የወታደራዊ ኢንዱስትሪ አካላት በስፋት የተካፈሉ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የመከላከያ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
በዚሁ ኮንፈረንስ ላይ ንግግር ያደረጉት ኢ/ር አይሻ መሀመድ ፈጠራን ፣ስትራተጂካዊ ውይይትንና በመከላከያ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ትብብርን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽኑ ዓለም አቀፋዊ ደህንነትን ለማጠናከር፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለመጠቀምና ትርጉም ያለው ትብብርን ለመፍጠር ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እና ህንድ ባለፉት አስርት ዓመታት የተጠናከረ ወታደራዊ የትብብር ታሪክ ያላቸው መሆኑን ገልፀው ከኢትዮጵያ ጋር በወታደራዊ በአቅም ግንባታ፣ በእውቀት ልውውጥና በቴክኖሎጂ ሽግግር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
በነገው ዕለትም የሁለቱን አገሮች ወታደራዊ ግንኙነት ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የታመነበት የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚካሄድ ኢዜአ ከስፍራው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።