የሃይማኖት ተቋማት ለምክክሩ ስኬታማነት እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል- ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት ተቋማት ለምክክሩ ስኬታማነት እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል- ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦-የሃይማኖት ተቋማት ለሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ስኬታማነት እያደረጉት ያለውን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ጋር በምክክሩ ሂደትና ተሳትፎ ዙሪያ ዛሬ ውይይት አድርጓል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት አመታት ለሰራው ስራና ላስመዘገበው ውጤት የሃይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ እንደነበር አውስተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ስኬታማ ውጤቶችን እንዲያስመዘግብ የሃይማኖት ተቋማት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይ የሚደረገው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን የሃይማኖት ተቋማት የተለመደውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኮሚሽኑ በሶስት ዓመታት ጉዞ ያከናወናቸውን ስራዎችና ቀሪ ተግባራትን አስመልክቶ ለኃይማኖት አባቶች ገለጻ አድርገዋል።
በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የሃይማኖት ተቋማት የሚሳተፉበት የአሰራር ሥርዓት ምክረ ሀሳብ ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የሃይማኖት አባቶች ኮሚሽኑ በብዙ ፈተናና ውጣ ውረድ ውስጥ ሆኖ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን እየተወጣ ላለው ታሪካዊ ኃላፊነት አድንቀዋል።
ከቀረበው የአሰራር ስርዓት ምክረ ሀሳብ በመነሳት በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የኃይማኖት ተቋማት ሊሳተፉ የሚችሉበትን ሁኔታ በምክር ቤታቸው በኩል ወስነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለኮሚሽኑ እንደሚያሳውቁም ጠቁመዋል።
በውይይቱ ላይ ከሃይማኖት አባቶች ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የኮሚሽኑ አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከውይይቱ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለሀገራዊ ምክክሩ ግብዓት እንዲሆኑ ያዘጋጀቻቸውን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ማስረከቧን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።