በአዳማ ከተማ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የተተገበረው የተቋማት ሪፎርም ውጤታማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የተተገበረው የተቋማት ሪፎርም ውጤታማ ነው

አዳማ፤የካቲት 4/2017 (ኢዜአ)፦የአዳማ ከተማ አስተዳደር የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የተገበረው የተቋማት ሪፎርም ውጤታማ መሆኑን የከተማዋ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ መኩሪያ ድንቁ እንዳሉት፥ ፅህፈት ቤቱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተደጋጋሚ የሚነሳባቸውን ተቋማት ለይቶ መፍትሄ ላይ አተኩሯል።
በዚህም የሰው ሀይል አደረጃጀትን በማሻሻልና የአገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ በማድረግ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ ስራ አስገብቷል።
ከተማ አስተዳደሩ የተገበራቸው የሪፎርም ስራዎችም ብልሹ አሰራሮች ለማስተካከል እገዛ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
በተለይም የዕለት ተዕለት የህዝብ አገልግሎት የሚበዛባቸው እንደ የመሬት አስተዳደር፣የገቢ፣የንግድ፣የኢንቨስትመንት፣የትራንስፖርት ተቋማት ወደ ዲጂታል አገልግሎት መግባታቸውን አንስተዋል።
እየተሰጠ ያለው የዲጂታል አገልግሎት የተገልጋዮችን እርካታ እያሳደገ የምልካም አስተዳደር ጥያቄም እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዚህም መንግስትና ህዝብ እንዲቀራረብ፣ግልጽነት እንዲኖርና ብልሹ አሰራር ለመቅረፍ ትልቅ አቅም መፍጠሩን አስረድተዋል።
በከተማ ደረጃ የተጀመረው አሰራር በክፍለ ከተሞችና በወረዳዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ መኩሪያ አክለዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የከተማ አስተዳደሩ ተገልጋዮች መካከል አቶ ኪያ ቡታ እንደገለጹት፥ቀደም ሲል ተበታትነው የነበሩ ተቋማት አሁን በአንድ ቦታ አገልግሎት እየሰጡ ነው።
በዚህም አገልግሎት አሰጣጡ ጊዜ የቆጠበላቸው ሲሆን ከአላስፈላጊ ወጪም እንደታደጋቸው ተናግረዋል።
አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል መስጠቱ ከዚህ በፊት የነበረን መንገላታት ያስቀረ ነው'' ያሉት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መቶ አለቃ ጃራ ኤባ ናቸው።
አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በአንድ ማእከል መገኘታቸው ብልሹ አሰራር ለማስወገድም እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።