በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ ነው
መቀሌ፤ የካቲት 3/2017(ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑ ተገለጸ።
የግብርና ሚኒስቴርና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የዘርፉ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ባለሙያዎች በክልሉ እየተከናወነ ያለውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በኃውዜን ወረዳ እና በሌሎች አካባቢዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል በግብርና ሚኒስቴር የዘላቂ ልማትና የመሬት አያያዝ የክትትልና ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ ፈታ ዘበርጋ፤ እየተከናወነ ያለው ስራ አስደናቂ በመሆኑ ለሌሎች አካባቢዎችም ጥሩ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው በርካቶችን ባሳታፈ መልኩ በአጭር ጊዜ በጥራትና በፍጥነት መሰራቱንም አድንቀዋል።
በመሆኑም በክልሉ እየተከናወነ ያለው የተቀናጀና አሳታፊ የሆነ የልማት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን አንስተዋል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አለምብርሀን ሀሪፈዮ፤ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮው የልማት መርሃ ግብር ከ62 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የሚከናወንበት መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው በተለይም የክልሉ አርሶ አደሮች በስፋት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰው በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።
በሐውዜን ወረዳ በልማት ስራው ላይ ከተገኙት አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ ፅገ ገብረ ክርስቶስ እና አቶ ዳንኤል ገብረ ኪዳን፤ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ለአርሶ አደሩ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በመገንዘብ ጠንካራ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።