ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ስፖርትን ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ስፖርትን ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው
አርባ ምንጭ፤ የካቲት 3/2017(ኢዜአ)፡- ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ስፖርትን ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ገለጹ።
"ለሀገራችን ስፖርት ዕድገት የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሚና ማላቅ" በሚል መሪ ሃሳብ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ እንደገለጹት፣ ለዘርፉ ውጤታማነት ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።
በተለያዩ ስፖርቶች ብቁ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚና ሌሎች ባለድርሻዎች ጉልህ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባም ገልጸዋል።
የስፖርቱ ዘርፍ ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ተገቢውን ሚና መጫወት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ምክር ቤቱ በስፖርት ዘርፍ ያለው ስብራት እንዲጠገን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑንና ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
በሳይንሳዊ ስልጠና ታንጸው ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ የሚያደርጉ ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት አካዳሚዎች፣ ትምህርት ቤቶችና ክለቦች ለታዳጊዎች ይበልጥ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።
በመድረኩ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፣ በስፖርት ኢንዱስትሪው የሚፈለገውን የሰው ሃይል ለማፍራት ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።
የስፖርት አካዳሚዎች የስፖርት ኢንዳስትሪን ያገናዘበ ጥናትና ምርምር በማድረግ ለዘርፉ ዕድገት እንዲሰሩም አስገንዝበዋል።
ተሰጥኦ ላላቸው ወጣቶችና ለስፖርት ሙያተኞች ሳይንሱን የተከተለና ወቅቱን ያገናዘበ ስልጠና መስጠት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
አቅምን አሟጦ በመጠቀም በሀገር፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘርፉን ለማሳደግ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አምበሳው እንየው ናቸው።
አካዳሚው ከ2009 እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ 531 ሠልጣኞችን በ10 የስፖርት አይነቶች አስተምሮ ማስመረቁን ገልጸዋል።
ለሁለት ተከታታይ ቀናት እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ላይ የፌዴራልና የክልል አመራር አባላት፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች፣ ተጋባዥ እንግዶችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።