የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የትራንስፖርት ዘርፍ ተዋናዮችን የሚያገናኝ የዲጂታል መተግበሪያ አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የትራንስፖርት ዘርፍ ተዋናዮችን የሚያገናኝ የዲጂታል መተግበሪያ አስጀመረ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2017(ኢዜአ)፦በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ የዲጂታል መተግበሪያ አስጀምሯል።
በማሪታይም ባለስልጣን ስትራቴጂና ፖሊሲዎች ውስጥ ከተጠቅሱ የመፍትሄ ሃሳቦች ውስጥ በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋሉ የድለላና የቅንጅት ጉድለቶችን መስመር በማስያዝ ተዋናዮችን የሚያገናኝ መተግበሪያ በማፍለቅ ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉ ተገልጿል።
በዚህም የትራንስፖርትና ሎጂስቲከስ ሚኒስቴር፣ የባለስልጣኑ፣ የግሉ ዘርፍ እንዲሁም በመንግስት-የግል አጋርነት የሚፈጸሙ 40 የሚደርሱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ፕሮጀክቶችን ጥቅም ላይ ማዋሉ ተገልጿል።
ፕሮጀክቶቹ በዘርፉ የመሰረተ ልማት ግንባታን፣ የአገልግሎት ማቀላጠፈያ ሥርዓትን፣ የጭነት እና የህዝብ ትራንስፖርት የአገልግሎት አቅም ግንባታ መርሃ ግብሮች የሚሳለጡበት እንደሆኑ ተነስቷል።
በዚህም መተግበሪያው በመንግስት ክትትል የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ያለውን የመረጃ ግንኙነት እና አገልግሎት የማሳልጥ የቴክኖሎጂ የአሰራር ሥርዓት መሆኑ ተመላክቷል።
መተግበሪያው በዩናይትድ አፍሪካ ሎጂስቲክስ የቴከኖሎጂ ኩባንያ እና ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሰራው ስኬታማ ተግባር የተቀናጀ የቴክኖሎጂ ሥርዓት "Digital Freight Marketplace systems" የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ እና ሌሎች የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ተዋናዮች ተገኝተዋል።