ቀጥታ፡

መንግሥት የዴሞክራሲ ተቋማት ጠንካራና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ የፈጠረውን ምቹ ምህዳር አጠናክሮ መቀጠል አለበት - ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2017(ኢዜአ)፡- መንግሥት የዴሞክራሲ ተቋማት ጠንካራና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ የፈጠረውን ምቹ ምህዳር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ገለጹ።

ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ የምርጫ ቦርድና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ መንግስት የህግና የአሰራር ማሻሻያዎችን አድርጓል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ኮሚሽኑ ለአሰራር አመቺ ያልነበሩ ህጎች ላይ ማሻሻያ ማድረጉን ገልጸዋል።

በተለይም ኮሚሽኑ በምርጫና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ስራውን በነጻነት እንዳይሰራ ያደርጉ የነበሩ የህግ ክፍተቶችን በማሻሻል በቂ ክትትል እንዲያደርግ የህግ ድጋፍ እንደተሰጠውም ነው ያነሱት።

ኮሚሽኑ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ላይ በነጻነትና በገለልተኝነት ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን መወጣት የሚያስችል የተሟላ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው መደረጉንም አንስተዋል።

እንደ ኮሚሽነር ብርሃኑ ገለጻ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት በምርጫ ወደ ስልጣን የሚመጣ መንግስት ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ናቸው።

ተቋማቱ ነጻነታቸውንና ገለልተኝነታቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ መደረጉ ለዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር የጎላ ሚና እንዳለውም ነው ያነሱት።

የለውጡ መንግሥት ወደ ስልጣን ሲመጣ እነዚህን ተቋማት ለማጠናከር የገባውን ቃል በተግባር ማረጋገጡን አድንቀዋል።

የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻነትና ገለልተኝነት እንዲጠበቅ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በቀጣይ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር በስፋት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 22/2017 ዓ.ም ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ አቶ ብርሃኑ አዴሎን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሸነር አድርጎ መሾሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም