የሕብረቱን ኮሚሽን ሊቀመንበርና ኮሚሽነሮች ማን ይተካቸው ይሆን? - ኢዜአ አማርኛ
የሕብረቱን ኮሚሽን ሊቀመንበርና ኮሚሽነሮች ማን ይተካቸው ይሆን?
አፍሪካዊያን ርዕሰ መንግስታት በየዓመቱ የሚመክሩበት የአህጉሪቷ ቁንጮ መድረክ ነው-የሕብረቱ መሪዎች ጉባዔ። በያዝነው ሳምንት መጨረሻ የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም ይደረጋል።
አፍሪካ-አቀፍ ዕቅዶችና ስኬቶች የሚገመገሙበት፣ የሚዘከሩበትና የሚመከርበት ወሳኝ ሁነት ነው። ለ38ኛ ጊዜ የሚደረገው የዘንድሮው የመሪዎች ጉባዔ “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።
ከመሪዎቹ ጉባዔ ቀደም ብሎ 46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ይደረጋል። የአፍሪካ ሕብረት የ2025 መሪ ቃል፣ የሕብረቱ ተቋማዊ ማሻሻያ ሪፎርሞች፣ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ለማግኘት የያዘቸው ውጥን፣ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ትስስር፣ ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የምግብ ዋስትና ጉባዔው የሚመክርባቸው አንኳር አጀንዳዎች ናቸው።
ከአህጉራዊና ቀጣናዊ አጀንዳዎች ባሻገር የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ጉዳይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የከፍተኛ ባለስልጣናት ምርጫ ነው። የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም በኮሚሽኑ ስር የሚገኙ ስድስት ኮሚሽነሮችን ምርጫ ይካሄዳል። ተመራጮችም የሃላፊነት ዘመናቸው የሚያጠናቅኑ አመራሮች ይተካሉ
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ዕጩዎች በየቀጣናው በተሰጠው የዕጩነት ኮታ መሰረት ለሕብረቱ አስገብተዋል። የዕጩዎች የማቅረቢያ ጊዜ የተጠናቀቀው ሐምሌ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ነበር።
ዕጩዎች የትምህርት ማስረጃቸው፣ የአፍሪካን የለውጥ አጀንዳ እንዴት ውጤታማ ማድረግ እንደሚችሉና አህጉሪቷ እያገጠሟት ያሉ የቆዩና አዳዲስ ፈተናዎችን በምን መልኩ ለመፍታት እንዳሰቡ ከሚያሳይ የራዕይ መግለጫ ሰነድ ጋር አቅርበዋል።
ማዕከላዊ፣ ምስራቅ፣ ደቡብ፣ ምዕራብና ሰሜን ዕጩ የሚቀርብባቸው የምርጫ ቀጣናዎች ናቸው። ኢትዮጵያዊቷ አንጋፋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስን ጨምሮ ከአምስቱ ቀጣናዎች የተወጣጣ አምስት አባላት ያሉት ቡድን ደግሞ የቀረቡ ዕጩዎች ያጣራል። ከአምስቱ ቀጣናዎች ጊዜ ጠብቆ በሚቀያየረው የዕጩ ማቅረቢያ መርህ አለ። በዚህም የዘንድሮው የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ዕጩ ከምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሆኗል። የሕብረቱ ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ደግሞ ከሰሜን አፍሪካ ይመረጣል። የዕጩዎች ማንነትም ታውቋዋል።
በዚህም መሰረት የጅቡቲ የውጭ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሐሙድ አሊ የሱፍ፣ የኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና የማዳጋስካሩ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ በኮሚሽኑ ዕጩ ሊቀ መንበር ሆነው ለምርጫ ቀርበዋል።
ባለፈው ወርሃ ታህሳስ 2017 ዓ.ም የምርጫ ክርክር ያካሄዱ ሲሆን ዕጩዎቹ የስራ ዕቅዳቸውን የትኩረት ነጥቦችም አቅርበዋል።
የጅቡቲ የውጭ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሐሙድ አሊ የሱፍ የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሆነው ቢመረጡ በሰላም እና ደህንነት በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ሌላኛው ዕጩ የኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነር ሆነው ቢመረጡ የሕብረቱ መስራች አባቶች ሕልም የሆነውን አፍሪካን አንድ የማድረግ ውጥን ማሳካት ዋነኛ ትኩረታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የማዳጋስካር የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆነው ቢመረጡ አካታች የፋይናንስ ተደራሽነት እንዲፈጠርና የዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰሩ በክርክሩ ወቅት አንስተው ነበር።
ከዕጩዎቹ አንዱ ከእ.አ.አ 2017 አንስቶ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የ64 ዓመቱ የቻድ ፖለቲከኛ እና ዲፕሎማት ሙሳ ፋቂ ማህማት መንበረ ስልጣን ይረከባሉ።
በሕብረቱ ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ከሰሜን አፍሪካ ይመረጣል። በዚሁ መሰረት ሳላህ ፍራኒስስ አልሃምዲ እና ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ ከአልጄሪያ፣ ሃናን ሞርሲ እና መሐመድ አህመድ ፋቲ ከግብጽ፣ ናጃት አል-ሃጃጂ ከሊቢያ እና ላቲፋ አክሃርባች ከሞሮኮ በዕጩነት ቀርበዋል። ከቀረቡ ዕጩዎች መካከል ተመራጩ ሰው የወቅቱን የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋ (ዶ/ር) ይተካል። የ53 ዓመቷ ሩዋንዳዊት ሞኒክ(ዶ/ር) የምጣኔ ሀብት ባለሙያ፣ ፖለቲከኛ እና ዲፕሎማት ሲሆኑ በምክትል ሊቀመንበርነት የተመረጡት በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2021 ነበር። የመጀመሪያዋ ሴት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ናቸው።
በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ስር የሚገኙ የስድስት ኮሚሽነሮች ምርጫ ይካሄዳል። እነሱም የግብርና፣ገጠር ልማት፣ “ብሉ ኢኮኖሚ “ እና ዘላቂ ከባቢ አየር፤ የኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ፣ኢንዱስትሪና ማዕድን፤ የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን፤ የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ፤ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት እንዲሁም የጤና፣ ሰብአዊ ጉዳዮችና ማህበራዊ ልማት ናቸው። ስድስቱ ኮሚሽነሮች ምርጫ ከማዕከላዊ፣ ደቡብና ምዕራብ አፍሪካ ቀጣናዎች ነው። ለስድስቱ ኮሚሽነሮች ዕጩዎችን ቀርበዋል።
በዚህም መሰረት
1. የ’ግብርና ገጠር ልማት ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ከባቢ አየር’ ኮሚሽን በአንጎላዊቷ ጆሴፋ ሳኮ፤
2. የኢኮኖሚ ልማት፣ የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽን - በዛምቢያዊው አልበርት ሙቻንጋ፤
3. የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽን - በአልጄሪያዊው ፕሮፌሰር መሐመድ ቤልሆሲን፤
4. የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽን - በግብጻዊቷ አማኒ አቡ-ዘይድ የሚመራ፤
5. የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽን - በናይጄሪያዊው አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ፤
6. የጤና፣ ሰብአዊ ጉዳዮችና የማህበራዊ ልማት ኮሚሽን - በቡርኪናፋሷዊቷ አምባሳደር ሚናታ ሳማቴ ሴሱማ እየተመራ ይገኛል።
አንድ የኮሚሽኑ አመራር ለአራት ዓመት የሚያገለግል ሲሆን አመራር ለመሆን በሚደረግ ምርጫ በድጋሚ ለመመረጥ መወዳዳር እንደሚችል የሕብረቱ መተዳደሪያ ደንብ ያመለክታል።
በቀረቡ ዕጩዎች መሰረት የሕብረቱ መሪዎች ጉባዔው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር እና ምክትል ሊቀ መንበርን ይመርጣል። የየሀገራቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ያቀፈው የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ ደግሞ ስድስቱን ኮሚሽነሮች ይመርጣሉ።
የሕብረቱን ቁልፍ የአመራርነት ቦታዎች እነማን ይቆናጠጡ ይሆን?