ቀጥታ፡

ለአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚና የመሪዎች ጉባኤ በቂ ዝግጅት ተደርጓል- የጸጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል

አዲስ አበባ፤ የካቲት3/2017(ኢዜአ)፦38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 46ኛው የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን አስታወቀ።

የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል እስከ አሁን ድረስ በአዲስ አበባና በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የተከናወኑ የፀጥታ ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን ገምግሟል።


 

38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 46ኛው የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በሰላም እንዲጠናቀቅ አዳዲስ ሎጅስቲክ አቅሞችን በመጠቀም ፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፀጥታ ኃይል በማሰማራት በቴክኖሎጂ የታገዘ የፀጥታና የደኅንነት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል።

በተከታታይ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያፌዴራል ፖሊስ፤ ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት፣ የሪፐብሊካን ጋርድ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና ሌሎች አጋር የፀጥታ አካላት የተቀናጀ ኦፕሬሽን አዲስ አበባ ከተማ ፍፁም ሰላማዊ ሆና እንድትቀጥል ያስቻለ መሆኑን ገልጿል።

አሁን ላይ የከተማዋ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ መቀጠሉን በግምገማው ያረጋገጠ መሆኑን ያመላከተው የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል ባካሄደው ግምገማ ለተገኘው ሰላም እና በተካሄደው ኦፕሬሽን ለመጣው ውጤት የህዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ነበረ ብሏል።


 

አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ሕብረት እና የተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ ፀጥታዋ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥልም ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ በግምግማው ተነስቷል።

እንደ ሀገር ሁሉም የፀጥታ መዋቅር የሚመለከተውን የሥራ ድርሻ ወስዶ አካባቢውን ፍፁም ሰላማዊ ለማድረግ በኃላፊነትና በተጠያቂነት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይሉ ጨምሮ ገልጿል።

በጉባኤው ላይ የሚታደሙ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ወግና ባህል በመቀበልና በማስተናገድ በቆይታቸው ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ፤ ካረፉባቸው ሆቴሎች ወደ መሰብሰቢያ አዳራሽ በሚሄዱበት ወቅት ሰላም ወዳዱ ሕዝባችን በባለቤትነት የሚጠበቅበትን የዜግነት ድርሻውን በኃላፊነት እንዲወጣ የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይሉ ጠይቋል።

ለፀጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ቀና ትብብርም አጠናክሮ እንዲቀጥል የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል ጥሪ ማቅረቡን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም