ለኢትዮጵያ ስፖርት ልማት ውጤታማነት አካዳሚው ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ስፖርት ልማት ውጤታማነት አካዳሚው ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ
አርባምንጭ፤ የካቲት 3/2017(ኢዜአ)፡- ለኢትዮጵያ ስፖርት ውጤታማነት አካዳሚው ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ለሀገሪቱ የስፖርት ውጤታማነት የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ላለፉት 10 ዓመታት ጉልህ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
በተለያዩ የስፖርት አይነቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ያደረጉ በርካታ ስፖርተኞች ማፍራቱንም ተናግረዋል።
የስልጠና፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማማከርና ተቋሙን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
ሚኒስቴሩ የስፖርት ልማትን ለማጠናከር የሚያግዙ ተቋማትን በማቋቋም ተከታታይነት ያለው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ለተተኪ ወጣቶች እንዲሰጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ አምበሰው እንየው በበኩላቸው አካዳሚው ብቃት ያላቸው ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በ10 የስፖርት አይነቶች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በዚሁም በሀገር፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ድል ያስመዘገቡ ተተኪ ወጣቶችን ማፍራት ተችሏል ነው ያሉት።
ባለፉት 10 ዓመታት ዘጠኝ ጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን የስፖርት ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ ሃሳቦችን ማቅረብ መቻሉንም ገልጸዋል።
በሳይንሳዊ መንገድ ብቁ ዜጎችን በማፍራት ብሎም ህዝባዊ መሠረት ያለው የስፖርት ልማት በመገንባት የህብረተሰብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተዘጋጀው የምክክር መድረክ የክልል አመራር አባላት፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻዎች እየተሳተፉ ነው።