ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የሚደነቅ ነው - ዓለም አቀፍ ተቋማት

አዲስ አበባ፤ የካቲት 03/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሰጠችው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑን ዓለም አቀፍ ተቋማት ገለጹ።

በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣናዊ የትብብር ማዕከል የካርቦን ግብይት ስፔሻሊስት አርባንስ ቤኒዋኒራ፤ ኢትዮጵያ አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሚናዋን እየተወጣች ነው ብለዋል።

የ2015ቱ የፓሪስ ስምምነት አንቀፅ-6 ለዓለም አቀፍ የካርበን ገበያና የልቀት ቅነሳ ትብብር ስትራቴጂ ማዕቀፍ መነሻ ነው ብለዋል።

በተማከለና በሁለትዮሽ ስምምነት ሀገራት የአየር ንብረት ኢላማን ለማሳካት ተግባራዊ የሚያደርጉት የአሰራር ሥርዓት የሚመራውም በዚሁ አንቀጽ መሰረት እንደሆነ አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ በአረንጓዴ አሻራና በታዳሽ የኃይል አማራጭ ዘርፍ ስኬታማ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እየገነባች መሆኗ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ለሞተር አልባና በኤሌክትሪክ ለታገዘ የትራንስፖርት ስርዓት ትኩረት መስጠቷ ለዓለም አቀፍ ስምምነቶች ትግበራና ለበካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም አንስተዋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአየር ንብረት ዙሪያ ጥናትና ማማከር ላይ የተሰማራው የክላይሜት ፐርሰፕሽን ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ስቴፈን ኖክ፥ በሞሮኮ እ.አ.አ በ2016 በተካሄደው የኮፕ-22 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የካርቦን ግብይት አሰራር ሥርዓት እንዲፈጠር ተሳትፎ ካደረጉ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ የካርቦን ገበያ ስትራቴጂ እያዘጋጀች መሆኗን አድንቀው ለተግባራዊነቱ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ፖሊሲና ማማከር አገልግሎት በኩል የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያርጉ ገልጸዋል።

ስትራቴጂው በፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት መሰረት የሀገሪቱን ዕምቅ አቅም ለመጠቀም እንደሚያግዝም ነው የጠቆሙት።

በታዳሽ የኃይል አማራጭ ላይ የሚሰሩ የልማት ስራዎች ለዜጎች ጤናማ ከባቢ በመፍጠርር የማይተካ ሚና እንደሚኖረውም አስገንዝብዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም