ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ላይ የሚመክር መድረክ እየተካሄደ ነው

አርባምንጭ፤ የካቲት 03/2017 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ላይ የሚመክር የባለድርሻ አካላት ምክክር መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው መድረክ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና የስፖርት ማህበረሰብ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የአካዳሚው ህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አላምረው ማሞ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት መድረኩ የተዘጋጀው የአካዳሚው የ10 ዓመት ጉዞ በመገምገም ለቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው።

May be an image of 1 person, smiling and eyeglasses

በዚሁ መሠረት የተቋሙ የ10 ዓመት የተልዕኮ ውጤታማነት፣ የሠልጣኞች ውጤታማነትና ፋይዳ እና የኢትዮጵያ ስፖርት መሠረታዊ ዕውቀት ለአመራሮች በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ሦስት ሰነዶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ብለዋል።

አካዳሚው ለሀገር አቀፍና ለዓለም አቀፍ ውድድሮች በአካልና በአዕምሮ የዳበሩ እንዲሁም በስነ-ምግባር የታነጹ ምርጥ ወጣት ስፖርተኞችን የማፍራት ተልዕኮ አንግቦ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት እና ጥናትና ምርምር እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው መድረኩ ውጤቱ ላይ ትኩረት አድርጎ ይመክራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም