ቀጥታ፡

አፍሪካውያን የ2063 አጀንዳዎችን ለማሳካት በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ መንቀሳቀስ አለባቸው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2017(ኢዜአ)፡- አፍሪካውያን የ2063 አጀንዳዎችን ለማሳካት በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው የዓለም ጥቁር ህዝቦች የታሪክ ቅርስ እና ትምህርት ማዕከል አስታወቀ፡፡

አፍሪካ በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን የህዝቧን ፍላጎት እና አህጉራዊ መሻትን እንዲሁም ተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ አጀንዳ 2063ን በመተግበር ላይ ትገኛለች።

የዓለም ጥቁር ህዝቦች የታሪክ ቅርስ እና ትምህርት ማዕከል ምክትል ፀሐፊና በደቡብ አፍሪካ የዋልተር ሲሱሉ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሊቪያ ንክንዩዛ፥ አፍሪካ ያላት ሀብት ከራሷ አልፎ ለሌሎችም የሚተርፍ ነው ብለዋል።

እምቅ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ጸጋዎቿን በመጠቀም አህጉራዊ ትልሞችን ለማሳካት በህብረቱ የተያዙ እቅዶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

የአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳዎች በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ተሰናስለው ከተተገበሩ ውጤታማ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

አፍሪካ እንደ አህጉር ከፍተኛ የወጣት ኃይል እና የተፈጥሮ ሀብት ያላት ብትሆንም ይህንን በእውቀትና በክህሎት ከመጠቀም ጋር ተያይዞ ክፍተቶች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

እነዚህን ክፍተቶች ማስተካከል የሚቻለው አህጉሪቱን የሚመጥን የትምህርት ስርዓት በመዘርጋት በመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም አፍሪካውያን በአህጉራቸው ያለ ቪዛ የሚንቀሳቀሱበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዲሁም ችግሮችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላም ማስፈን ከቻሉ የ2063 አጀንዳ መሳካቱ አይቀሬ ነው ይላሉ፡፡


 

ከዓለም ጥቁር ህዝቦች የታሪክ ቅርስ እና ትምህርት ማዕከል መስራቾች አንዷ የሆኑት ቦይቱሜሎ ሞኖኬሲ በበኩላቸው፥ አፍሪካውያን የ2063 አጀንዳዎችን ለማሳካት ከሁሉም በላይ አንድነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ አህጉር የተያዘው አጀንዳ ወቅቱን የሚመጥን ከመሆኑም በላይ በአፍሪካ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት የሚፈታ ቢሆንም አተገባበሩ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም አህጉራዊ አጀንዳዎችን ለማሳካትና የአፍሪካን ትንሳኤ ለማብሰር ትብብርን ማጠናከርና ችግሮችን በጋራ መሻገር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም አህጉሪቱ ከተረጂነት በመላቀቅ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን እንድታረጋግጥ በፓንአፍሪካዊ እሳቤ የተቃኘ የተግባር ምዕራፍን ማጠናከር የግድ ነው ብለዋል።

በዚህም የምንመኛትን አንድነቷ የጠነከረ እና የበለጸገች አፍሪካን እውን ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም