የሀገራቱ መሪዎች የአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ያሳዩት ቁርጠኝነት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራቱ መሪዎች የአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ያሳዩት ቁርጠኝነት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2017 (ኢዜአ)፦ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት መሪዎች የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ያሳዩት ቁርጠኝነት እና አጋርነት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ተግባር ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ (EAC) እና የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ (SADC) በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የጋራ የመሪዎች ስብሰባ በታንዛንያ ዳሬ ሰላም ተካሄዷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ በስብሰባው የተገኙ ውጤቶች እና ውሳኔዎችን በመልካም ጎኑ እንደምታያቸው ገልጿል።
ኢትዮጵያ የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሁሉ ሀሰን (ዶ/ር)፣ የኬንያ ፕሬዝዳንት እና የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ሊቀመንበር ዊሊያም ሩቶ(ዶ/ር) እና የዚምባቡዌ ፕሬዝዳንት እና የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ ሊቀመንበር ኤመርሰን ምናንጋግዋ ስብሰባው በስኬት እንዲጠናቀቅ ያሳዩት አመራር አድንቃለች።
ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የማበጀት መንፈስ ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ያሳዩት ትብብር እና ቁርጠኝነት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ተግባር ነው ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫው።