የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ የግልና የመንግስት አጋርነት ወሳኝ ሚና አለው - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ የግልና የመንግስት አጋርነት ወሳኝ ሚና አለው - ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ የግልና የመንግስት አጋርነት ወሳኝ ሚና እንዳለው ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
ያኔት ሆስፒታሎች በህክምናው ዘርፍ ዓለም አቀፍ የጥራት እውቅና ማግኘቱን በተመለከተ ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎትና ያኔት ሆስፒታሎች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ መንግስት የጤና ተቋማትን ማስፋት፣ የህክምና ባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት፣ ዘመኑ የሚጠይቀውን የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂን ማስረፅና በቂ የህክምና ግብዓቶችን የማሟላት ተግባራት እያከናወነ ይገኛል።
በተለይም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት መመዝገቡን አመልክተው፤ ከግሉ ዘርፍ ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከርም ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ያኔት ሆስፒታሎች የዓለም አቀፍ ጥራት እውቅና ማገኘታቸው፥ እንደ ሀገር የጤና አገልግሎት ጥራት እየተሻሻለ መምጣቱን እንደሚያመለክት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ቦንሳ ባይሳ በበኩላቸው፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በደረጃ፣ በጥራትና መሠል ጉዳዮች ያሉበትን ሁኔታ በሚመለከት በየወቅቱ የምዘናና የፍተሻ ስራ ይከናውናል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዘርፎች የተገልጋይ ጠያቂነትና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት የማግኘት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ የቁጥጥር ስራውን በእጅጉ እያገዘው መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የህክምና ተቋማት ዓለም አቀፍ ደረጃ የጥራት እውቅና ማግኘታቸው ለህክምና ዘርፉ ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥር አክለዋል።
የሊያና ኸልዝ ኬርና በስሩ የሚተዳደሩት የያኔት ሆስፒታሎች መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ግርማ አባቢ እንደገለጹት፤ መንግስት ለግል የህክምና ዘርፍ የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል አበረታች ነው።
ዓለም አቀፍ የጥራት እውቅና ማግኘታችንም ለላቀ አገልግሎት ያነሳሳናል ነው ያሉት።