ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር ብቁ ለመሆን ጠንክረን እንድንሰራ አነሳስቶናል-ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር ብቁ ለመሆን ጠንክረን እንድንሰራ አነሳስቶናል-ተሳታፊዎች
ሶዶ፤ የካቲት 1/2017 (ኢዜአ)፡-ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር ተስጧቸውን በአግባቡ በመጠቀም ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን ጠንክረው እንዲሰሩ ያነሳሳቸው መሆኑን ተወዳዳሪዎች ገለጹ።
በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የነበረው ውድድር ዘንድሮ በ11 የስፖርት ዓይነቶች መልሶ የተጀመረ ሲሆን የውድድሩ መጀመር ተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራት እንደሚያግዝም ተመላክቷል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተወዳዳሪዎች ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን ጠንክረው እንዲሰሩ ያነሳሳቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የቦክስ ስፖርት ተወዳዳሪ ወጣት መፍቱ ከድር "የታዳጊ ወጣቶች ውድድር ችሎታችንን እንድናወጣና እንድናሳድግ ይረዳናል" ብሏል።
ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመጡ ተወዳዳሪዎች ጋር መገናኘታችን ልምዶችን ከመቅሰም ባለፈ እርስ በርስ ለመተዋወቅና ተሰጧችንን አውጥተን ለማሳየት መነሳሳት ፈጥሮብናል ሲሉም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ደሴ ከተማ በመምጣት በውድድሩ የተሳተፈው ታዳጊ ወጣት ዛኪር አብዱልከሪም በበኩሉ፣ ውድድሩ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በውድድሩ የተለያየ ብቃት ያላቸውና ለሀገር ጭምር ተስፋ የሚሆኑ ታዳጊዎችን ማየቱን ጠቅሶ፣ ውድድሩ የሚፈጥረውን የአቅም ማሳደግ ዕድል በመጠቀም በቀጣይ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ መነሳሳቱን ገልጸዋል።
"እንደአገር ከአትሌቲክስ በስተቀር በሌሎች የስፖርት አይነቶች ብዙ ውጤት ያልታየው በታዳጊዎች ላይ ባለመሠራቱ ነው" ያለው ደግሞ በእግር ኳስ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተወካይ ታዳጊ ዮናታን ኢያሱ ነው።
የተጀመረው የታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር ኢትዮጵያ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች በአህጉርና በዓለም አቀፍ መድረኮች ጎልታ እንድትወጣ እንደሚያግዝም ተናግሯል።
የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የትምህርትና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያና የስፖርተኞች ቡድን መሪ አቶ አብዶ ሙሜ "ውድድሩ ታዳጊዎች ራሳቸውን የሚያዩበትና ልምድ የሚቀስሙበት ነው" ብለዋል።
በየክልሉ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች በታዳጊዎች ላይ ትኩረት አድርገን ከሠራን የኢትዮጵያ ስፖርት ለማንሰራራት ብዙ ጊዜ አይፈጅም ሲሉም ገልጸዋል።
"የታዳጊ ስፖርተኞች ልማት ለአሸናፊ ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ያለው 8ኛው ሀገር አቀፍ የታዳጊ ስፖርተኞች ምዘና ውድድር ቀጥሏል።
በውድድሩ ከ2 ሺህ 600 በላይ ተወዳዳሪዎች በ11 የስፖርት ዓይነቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡