ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የማህበረሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ይዘቶችን ማጠናከር አለባቸው - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- መገናኛ ብዙሃን የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የማህበረሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ይዘቶችን ማጠናከር እንዳለባቸው የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ተጨባጭ ተግባራትን እያከናወነች እንዳለችም ተጠቅሷል።

ሚኒስቴሩ በተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ እና አስተዳደር፣ ዘላቂ የቡና ሃብት ልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የደን ሀብትና የስነ-ህይወት ጥበቃ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በቢሾፍቱ ስልጠና እየሰጠ ነው።


 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በፖሊሲ የተደገፉ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

በበጋ ወራትም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና የተፋሰስ ልማትም ማህበረሰቡን በማሳተፍ በስፋት እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል።

ይህም የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግና የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የተፈጥሮ ሚዛን እንዲስተካከል እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ለታዳሽ ኃይል ልማት ትኩረት መስጠቷንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያብራሩት።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖው ድንበር ዘለል በመሆኑ የመከላከል ስራውም ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ይሻል ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ በቂ ግንዛቤ በመያዝ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አንስተዋል።

በዚህም በተጨባጭ መረጃዎች ላይ በመመስረት የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለሚያሳድጉ ይዘቶች ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም