ቀጥታ፡

መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ጥረት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፦ መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ግጭቶች በውይይት እና ድርድር እንዲፈቱ እያደረገ ያለው ጥረት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ምክትል ጠቅላይ ጸሐፊ ሓጂ መስዑድ አደም ገለጹ፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ከጥር 23 እስከ 25 በአዲስ አበባ ያካሄደው ሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ መጠናቀቅን ተከትሎ ባወጣው የአቋም መግለጫ ዘላቂና አወንታዊ ሰላም የሀገሪቱ የህልውና መሠረትና የሁለንተናዊ ብልጽግና ዓይነተኛ ዋስትና መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

ፓርቲው የተጀመረው አካታች ሀገራዊ ምክክር በስኬት ተጠናቆ የኢትዮጵያን የዘመናት የፖለቲካ ስንክሳር እንዲዘጋ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ጠቁሟል፡፡

አወንታዊ ዘላቂ ሰላምን እያስተጓጐሉ ከሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች ጋር የሚደርገው ውይይትና ድርድር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ተጨማሪ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡንም አክሏል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ምክትል ጠቅላይ ጸሐፊ ሓጂ መስዑድ አደም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛው ጉባኤ ያስቀመጣቸው የአቋም መግለጫዎች በሀገሪቱ ሰላምን በማስፈን ዕድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አላችው ብለዋል።

በመሆኑም መንግስት ጥያቄዎችን ከሀይል አማራጭ ይልቅ በውይይት እና በድርድር ለመፍታት ከዚህ ቀደምም የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህም መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ግጭቶች በውይይት እና በድርድር እንዲፈቱ እያደረገ ያለው ጥረት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል።

መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እያደረገ ያለውን ጥረት ያደነቁት ሓጂ መስዑድ አደም፤ ይህም ለዘላቂ ሰላም ዋስትና የሚሰጥ ነው ብለዋል።

መንግስት ያቀረባቸውን የሰላም ጥሪዎች ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ህይወት የመጡ ታጣቂዎች ለህዝባቸው ትልቅ ውለታ የከፈሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ዘላቂ ሰላምን ከማጽናት አኳያ ያለውን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመው የሃይማኖት ተቋማትም ሰላም የዘወትር ስብከታቸው ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም