ለሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት ተሳትፏችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት ተሳትፏችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - ወጣቶች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት ተሳትፏቸውንና በጎ ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ወጣቶች ገለፁ።
በኢትዮጵያ ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታትና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር፣እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለመገንባት የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል።
ኮሚሽኑ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ እንዲሁም ወጣቶችን ጨምሮ በዋናው ሀገራዊ ምክክር የሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ልየታን አጠናቅቋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች በሀገራዊ ምክክሩ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ወጣት ዘላለም ዓለምነህ፥ ሀገራዊ ምክክሩ እንደሀገር እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ሁነኛ መንገድ ነው ብሏል።
በዚህም ወጣቶች ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለምክክር ሂደቱ ስኬት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁሟል።
ወጣት ዳቃ ቱጂባ በበኩሉ፥ ሀገራዊ ምክክሩ የሀገረ መንግስት ግንባታን ለማጠናከር መልካም እድል በመሆኑ ለስኬቱ የበኩሉን በጎ ሚና እንደሚወጣ ገልጿል።
ወጣቶች የነገ ሀገር መሪ በመሆናቸው ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡ አጀንዳዎች እንዲንሸራሸሩ በንቃት መስራት አለባቸው ያሉት ደግሞ ወጣት ይበልጣል አሰፋ እና ወጣት መሐመድ አሕመድ ናቸው።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ በበኩላቸው፥ የሀገራዊ ምክክር ዓላማ የተሻለች ሀገርን ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ ነው ብለዋል።
እንደሀገር ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ልማትን በማስቀጠል የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም ለስኬታማነቱ ወጣቶች በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ ለሰላምና ለተረጋጋ የሀገረ መንግስት ግንባታ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው።
እስካሁን ባለው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ወጣቶች የመነጋገር እና የመደማመጥ ባህልን በማጎልበት እያደረጉት ያለው ተሳትፎ አበረታች እንደሆነ ጠቅሰው፥ በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።