የመሪዎቹን ጉባዔ ከአንድ ሺህ በላይ ጋዜጠኞች ሽፋን ይሰጡበታል ተብሎ ይጠበቃል - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
የመሪዎቹን ጉባዔ ከአንድ ሺህ በላይ ጋዜጠኞች ሽፋን ይሰጡበታል ተብሎ ይጠበቃል - ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017 (ኢዜአ)፦ 38ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ከአንድ ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞች ሽፋን ይሰጡታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።
ጉባዔው “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ቃል የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን የአፍሪካ ህብረት ብሄራዊ የጉባዔ አመቻች ኮሚቴ አባል በመሆን ጉባዔው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅና የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል።
ስብሰባውን ለሚዘግቡ የሀገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች “ፕሬስ ፓስ” እንዲያገኙ ማድረግ፣ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የውጭ መገናኛ ብዙኃን አካላት የመዳረሻ ቪዛ የማመቻቸት እና ለሙያ መገልገያ መሳሪያዎቻቸው የከስተም ክሊራንስ መስጠት ከስራዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
ስራዎቹን ቀልጣፋ ለማድረግ በቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ጉምሩክ፤ በአፍሪካ ህብረት ባጅ ሴንተር እንዲሁም በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና መስሪያ ቤት የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ነው ባለስልጣኑ ያስታወቀው።
በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ከአንድ ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞች የሚዲያ ሽፋን ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክቷል።
እስከ አሁን 390 የሀገር ውስጥ እና 530 የውጭ ጋዜጠኞች መመዘግባቸውን የተቋሙ መግለጫ ያሳያል።
ጉባዔው የኢትዮጵያን መልካም ገፅታን አጉልቶ በማሳየት በስኬት እንዲጠናቀቅ ባለስልጣኑ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አስታውቋል።
ከመሪዎቹ ጉባዔ ቀደም ብሎ 46ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።