ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች ነው - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኗን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ሰላም ለጎረቤቶቿ ሰላም ወሳኝ እንደመሆኑ መጠን የጎረቤት ሀገራትም ሰላም የራሷ ሰላም መሆኑን በተግባር አረጋግጣለች።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ያክል ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ሚናዋን እየተወጣች ያለች ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ያደረገችው አስተዋጽኦ ለዓለም ሰላም ጭምር እንዳደረገችው የሚወሰድ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሀገራት ለሽብርተኝነት ሽፋን ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማረም እንደሚገባቸው ጠቁመው፤ ይህም ለአካባቢው ሀገራት የልማት፣ የእድገት እንዲሁም የሰላም ማረጋገጫ ምቹ መንገድ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደሩ አክለውም በቀጣናው ሠላም እንዲሰፍን ሀገራት ሽብርተኝነትን ለመከላከል በጋራ የሚያደርጉት ጥረት ዓለም አቀፍ ግንኙነታቸው ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚያስችል አንስተዋል።

ሰላምን በማወክ የአካባቢውን ሀገራት እድገት ወደ ኋላ ሊያስቀር የሚችለውን ሽብርተኝነትን ለማጥፋት በጋራ መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊትም ከወዳጅ ሀገራት ጋር በመተባበር ሰፋፊ ተግባራትን ስታከናውን መቆየቷን ነው አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም