ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ SWAT ቡድን አቀባበል ተደረገለት

አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ))፦ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች SWAT Challenge ላይ ሲወዳደር የቆየው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ SWAT ቡድን በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ስትራቴጂክ አመራሮች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እንደ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የፖሊስ ተቋም በተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች SWAT Challenge ውድድር ላይ መሳተፉ ለሀገራችን ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ጠቀሜታ ከማስገኘቱም ባሻገር ዓለም አቀፍ የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነትን ለማዳበር ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።


 

ኮሚሽነር ጀነራሉ በኢትዮጵያ የፖሊስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ መቻላችን ልምድና ተሞክሮ እንድናገኝ ያስቻለን ከመሆኑም በላይ በቀጣይ ለሚደረገው ውድድር መሻሻል የሚገባቸውን በመለየት በተሻለ ብቃት መዘጋጀት እንድንችል ዕድል የፈጠረ መሆኑን መናገራቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የSWAT ቡድን አባላት በሰጡት አስተያየት በSWAT Challenge ውድድር ላይ በቦታው በመገኘት ከሌሎች ሀገራት የSWAT ቡድን ጋር ልምምድ በማድረጋችን በመሰናክል ውድድር የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል፤ በቀጣይም እ.ኤ.አ 2026 በሚካሄደው የUAE SWAT Challenge ውድድር ላይ አስፈላጊውን ስልጠና በመውሰድ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትጋት እንሠራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ SWAT ቡድን ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሠርተፊኬት የተበረከተለት ሲሆን በቀጣይ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፍም የኢንቪቴሽን ካርድ ተሰጥቶታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም