ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ላጋጠሟት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች በበቂ ሁኔታ ምላሽ መስጠት ችላለች - ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ላጋጠሟት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች በበቂ ሁኔታ ምላሽ መስጠት መቻሏን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ ገለጹ።

የጤና ስርዓቱ በየጊዜው እየጨመሩ ላሉ የሕብረተሰብ የጤና አደጋዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዝግጁነት ሊኖረው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


 

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 10ኛውን የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ፎረም “የማይበገር የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስርዓት ለብሄራዊ ጤና ደህንነት” በሚል መሪ ሀሳበ በሃዋሳ ከተማ እያካሄደ ነው።

በፎረሙ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ፣ የክልል ጤና ቢሮ አመራሮች እና ሌሎች የተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ዶክተር አየለ ኢትዮጵያ ላጋጠሟት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች በበቂ ሁኔታ ምላሽ መስጠት መቻሏን ገልጸዋል።

ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዓለምን እየፈተኑ ያሉ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች እየተበራከቱና እንደ ሀገርም ፈተና እየሆኑ መምጣታቸውን አመልክተዋል።

የጤና ስርዓቱ ለአደጋዎቹ ምላሽ መስጠት የሚያስችለው ዝግጅት ሊኖረው እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።


 

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ ፎረሙ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ እና የቅንጅት አሰራርን ለማጎልበት ምቹ አጋጣሚን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የሕብረተሰብ የጤና አደጋዎችን ለመከላከል የመፍትሔ ሀሳቦችን ማስቀመጥ የሚያስችል መድረክ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ”የቤተሰብ ኃላፊነትና የማህበረሰብ አጋርነት ለሁሉም አይነት አደጋዎች አይበገሬነት!” በሚል ርዕስ የመነሻ ጽሁፍ አቅርበው ውይይት እንደተደረገበት ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም