ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የሙቀት መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የመንግስት የስራ ሰዓት ላይ ማሻሻያ ተደረገ

ጋምቤላ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል የሙቀት መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የመንግስት የስራ ሰዓት ላይ ማሻሻያ መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት ዛሬ እንደገለጹት የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱና ለስራ ምቹ ባለመሆኑ ከነገ የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ የመንግስት የስራ ሰዓት ለውጥ ተደርጓል።

በለውጡ መሰረትም ቀደም ሲል ከጧቱ አንድ ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ተኩል የነበረው ከአንድ ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት ተኩል እንዲሆን ተወስኗል።

እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከዘጠኝ ሰዓት እስከ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል የነበረው ከአስር ሰዓት እስከ አስራ ሁለት ሰዓት ተኩል እንዲሆን ተወስኗል ብለዋል።

የስራ ሰዓት ለውጡ ወይናደጋ የአየር ንብረት ያላቸውን የመንገሺና የጎደሬ ወረዳዎችን እንደማይጨምር የገለጹት ኃላፊው፤ የክልሉ የመንግስት ሰራተኞች በተጠቀሰው የተለመደውን ስራቸውን እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የጋምቤላ ክልል የሚትዎሮሎጂ አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋሁን ዓለሙ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የክልሉ አማካይ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን 39 ነጥብ 2 ዲግሪ ሴልሸስ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም የሌሊቱ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ደግሞ 23 ዲግሪ ሴልሸስ መድረሱን ጠቁመው፤ የሙቀቱ መጠን በቀጣዮቹ ሶስት ወራት አሁን ካለው ሊጨምር እንደሚችልም አመላክተዋል።

ባለፉት ወራት የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን 35 ዲግሪ ሴልሸስ፤ የሌሊቱ ደግሞ ከ21 ዲግሪ ሴልሸስ በታች እንደነበር አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም