ቀጥታ፡

በክልሉ የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት አፈጻጸም ማሻሻል ይገባል - ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት አፈጻጸም ለማሻሻል በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

የ2017 በጀት ክልል አቀፍ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት የንቅናቄ መድረክ ''የጤና መድህን አገልግሎት ለጋራ ተጠቃሚነት'' በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል።

በንቅናቄው ማስጀመሪያ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)፣ የክልሉ አስፈጻሚ አካላት፣ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎትና የክልሉ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የጤና መድህን አገልግሎት ሥራዎች አፈጻጸም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችን ቢያሳይም አፈጻጸሙ የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚነትና ተደራሽነት ማሳደግ ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ገልጸው ለዚህም አመራሩ አበክሮ እንዲሰራ አሳስበዋል።

May be an image of 6 people, newsroom and dais

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው በክልሉ በ48 የማህበረሰብ መድን ጤና ቋትና በ60 ወረዳዎችና ከተማ አስተደደሮች የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ 30 ሺህ 51 ግለሰቦችን አባል ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

በ2016 በጀት ዓመት 292 ሺህ 943 አባላትና ቤተሰቦቻቸው በጤና ተቋማት የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።

May be an image of 1 person, dais and newsroom

የህክምና አገልግሎት ለሰጡት ጤና ተቋማትም 102 ሚሊዮን 265 ሺህ 574 ብር ክፍያ መፈጸሙን ጠቁመዋል።

ቢሮው የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት አፈጻጸም እና ተደራሽነት ለማሻሻል እየሰራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም