ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመከላከል የሚያግዝ ረቂቅ አዋጅ አፀደቀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአካባቢና ማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ተጋላጭነትን ለመከላከል የሚያግዝ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

ምክር ቤቱ 18ኛ መደበኛ ስብሰባውን አድርጓል።


 

በስብሰባው ላይ የምክር ቤቱ የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሪት ፈቲያ አህመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመከላከል የሚያግዝ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።

ሰብሳቢዋ አዋጁ በማደግ ላይ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ዕድገት በአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት ላይ ጉልህ ጉዳት የማያስከትልና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት የማይበገር እንዲሆን የሚያስችል ሥርዓትን ለመዘርጋት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።


 

አዋጁ ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶችና ሕግጋት ጋር የሚጣጣም የሕግ ማዕቀፍ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም መገንባት ዘላቂ ልማት እና የህብረተሰብ ተሳትፎን ለማሳደግ ለሀገር ዕድገት ጉልህ ሚና እንደሚኖረውና በዚህ ረገድም ረቂቅ አዋጁ አጋዥ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ የአካባቢና ማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ረቂቅ አዋጁን በመመርመር በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም