ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ሳምንት መርሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።

የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በአዳማ ከተማ እና ሲዳማ ቡና መካከል ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።

አዳማ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ምንም ማሸነፍ አልቻለም።

ቡድኑ በ15 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ሲዳማ በአምስቱ ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ሶስት ግቦችን በማስተናገድ በ22 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በ19ኛ ሳምንት ሁለተኛ መርሃ ግብር ስሑል ሽሬ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ስሑል ሽሬ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች መካከል በአራቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ቡድኑ በጨዋታዎቹ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር ስምንት ጎሎችን አስተናግዷል። በሊጉ በ12 ነጥብ 17ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል። በቀሪዎቹ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።

ወልዋሎ በነዚህ ጨዋታዎች አራት ግቦችን ከመረብ ላይ በማስቆጠር  አምስት ጎሎች ተቆጥረውበት በሰባት ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃን ይዟል። 

የ19ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል። መቀሌ 70 እንደርታ እና ሃዋሳ ከተማ የሳምንቱ አራፊ ቡድኖች ናቸው።

ከ19ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በኋላ የሊጉ አንደኛ ዙር ውድድር ይጠናቀቃል።

ኢትዮጵያ መድን በ32 ነጥብ ሊጉን ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ29 ነጥብ ይከተላል።  መቻል እና ሀዲያ ሆሳዕና በተመሳሳይ 27 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ሃዋሳ ከተማ፣አዳማ ከተማ፣ ስሑል ሽሬ እና እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ15ኛ እስከ 18ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ፣ የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ እና የአርባምንጭ ከተማው አህመድ ሁሴን በተመሳሳይ ሰባት ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በጋራ እየመሩ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም