የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2017(ኢዜአ)፡- የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወር ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ በወረርሽኝና በወባ ምክንያት የሚፈጠር ሞትን ለማስቀረት የመከላከል ስራዎችን በተሻለ መልኩ ተደራሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ለዚህም የጤና ኤክስቴንሽን ስራዎችን በተለይም የወባ ወረርሽኝን ጨምሮ ውሃ ወለድ በሽታዎችንና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮችን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን ዲጂታላይዝ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለዚህም አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩትን በማጠናከር በምርምር በሚመጡ ውጤቶች ላይ በስፋት መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ(ዶ/ር) በበኩላቸው በወባ የሚሞተው የሰው ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ቁጥር ለመቀነስ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በተለይም በኮሌራ፣ በእብድ ውሻ በሽታ፣ በማጅራት ገትር እና ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ በሚመጣ በሽታ የሚፈጠረውን የስርጭትና የሞት መጠን ለይቶ እና አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ከታችኛው እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት ተመልክቷል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው የወባ በሽታ ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ዋነኛ የጤናና የማህበራዊ ቀውስ መንስኤ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገራችን በበሽታው በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ መሆኗን ተናግረዋል።
ወባን ከሀገራችን ለማጥፋት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እና ስትራቴጂ ተነድፎ በተመረጡ ወረዳዎች ላይ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንም አብራርተዋል።
በስድስት ወር ውስጥ 13 ነጥብ 9 ሚሊዮን ለሚሆኑ በወባ መያዛቸው ለተጠረጠሩ ህሙማን ምርመራ መደረጉን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሣይ ሀይሉ እንዳሉት የወባ ወረርሽኝ እንዳይዛመት ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች የመጡ ውጤቶችን መገምገም ተችሏል ብለዋል።
በዚህም በስድስት ወራት ውስጥ በበሽታው የሚያዙትን ቁጥር ሀምሳ በመቶ ለመቀነስ ዕቅድ ተይዞ ከሀምሳ ሁለት በመቶ በላይ መቀነስ እንደተቻለ ማስረዳታቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።