በህብረቱ ጉባኤ የኢትዮጵያን ባህላዊ ዕሴቶች የሚያንጸባርቅ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በህብረቱ ጉባኤ የኢትዮጵያን ባህላዊ ዕሴቶች የሚያንጸባርቅ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል
አዲስ አበባ፤ጥር 29/2017(ኢዜአ)፦በአፍሪካ ህብረት ጉባኤ የኢትዮጵያን ባህላዊ ዕሴቶች የሚያንጸባርቅ መስተንግዶና የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የቱሪዝም ሚኒስቴር አሰታወቀ።
38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም እንዲሁም 46ኛው የህብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ቀደም ብሎ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡
ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫና የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ ጉባኤውን በሰለጠነ የሰው ኃይል በመታገዝ በብቃት ለማስተናገድ በሁሉም መስክ ዝግጅት ማጠናቀቋም ተገልጿል።
በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ እንግዶችን ለማስተናገድ ለበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች፣ለተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ግለሰቦች ስልጠና በመስጠት መርኃ ግብሩን በስኬት ለማጠናቀቅ ሁለንተናዊ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
የህብረቱን ጉባኤ በላቀ መልኩ ለማስተናገድ በሁለንተናዊ ቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ባህላዊ ማንነት የሚያንጸባርቅ የአቀባበል ስነ ስርዓት እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል።
በመዲናዋ በዋና ዋና ጎዳናዎች በተሰቀሉ ግዙፍ ስክሪኖች አማካኝነት ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቁ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ማሳየትን ጨምሮ የከተማዋን ገጽታ የሚያጎላ ሳቢ ስነ ስርዓት እንደሚኖርም አክለዋል።
በመዲናዋ የሚገኙ ባለ ኮከብ ሆቴሎች ከእንግዳ አቀባበል ጀምሮ መስተንግዷቸውን የተሟላ በማድረግ ራሳቸውን እንዲያበቁ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል መደረጉን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባለፈ የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ባህል አጉልተው የሚያሳዩ ሁነቶችን አዘጋጅተው እንግዶቻቸውን እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና መሆኗን አጉልተው የሚያሳዩ ዝግጅቶችን እንዲያከናውኑ ያልተቋረጠ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
ለጉባኤው ተሳታፊዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ የሜትር ታክሲና መሰል አሽከርካሪዎች የአራት ቀናት ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
ስልጠናው እንግዶች ያለ ምንም እንግልት ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀሱ በማስቻል ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በከተማዋ በአዲስ መልክ የተሰሩ የልማት ስራዎችን እንዲጎበኙ የሚያስችል መርሃ ግብር መዘጋጀቱንም አክለዋል።
በተለይም የኮሪደር ልማት ስራውን በማስጎብኘት አዲስ አበባን የማስተዋወቅ እንደሚከናወን ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ጠቅሰዋል።