ፋይዳ የዲጅታል መታወቂያ የዜጎችን መብትና የሀገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ፋይዳ የዲጅታል መታወቂያ የዜጎችን መብትና የሀገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው
አዲስ አበባ፤ጥር 29/2017 (ኢዜአ)፦ፋይዳ የዜጎችን መብት የሚያስጠብቅ፣ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅም የሚያስከብር መሆኑን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ምክትል አስተባባሪ ራሄል ይትባረክ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው "ፋይዳ ለኢትዮጵያ" የተሰኘ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
በኢትዮጵያ የነዋሪዎችን የመታወቅ መብት ለማረጋገጥ፣ በአገልግሎት ሰጭና ተቀባዮች መካከል መተማመን እንዲዳብር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግልጽነት ተጠያቂነትና የተሳለጠ አሰራር ስርዓት ለማንበር የዲጅታል መታወቂያ ገቢራዊ ተደርጓል።
በዚህም የኢትዮጵያ ዲጅታል መታወቂያ በአዋጅ ቁጥር1284/2015 ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባ ሲሆን እስካሁን ከ12 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች የዲጅታል መታወቂያ ባለቤት ለመሆን ተመዝግበዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ምክትል አስተባባሪ ራሄል ይትባረክ በዚህ ወቅት፣
ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ እንደ ስሙ ሁሉ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
ፋይዳ የዜጎችን መብት የሚያስጠብቅ፣ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅም የሚያስከብር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበባ በርካታ ነዋሪ መመዝገቡን አንስተው፣ በክልሎች ለማስፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ዲጅታል መታወቂያ የአገልግሎት ሰጭና ተቀባዮችን በማስተሳሰር ቀልጣፋ የዲጂታል አገልግሎት መስጠት ያስችላልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የፋይዳ ለኢትዮጵያ ፕሮግራም በማዘጋጀቱ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፥ ኢዜአ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ተልዕኮ የተሰጠው የሀገሪቱ የዜና ወኪል መሆኑን ገልጸዋል።
አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠሩንም ተናግረዋል።
በዚህም የዜናና ዜና ነክ ፕሮግራሞችን ከማዘጋጀት ባለፈ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ሀገራዊ ተልዕኮውን እየተወጣ ነው ብለዋል።
በብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ላይ ያተኮረው "ፋይዳ ለኢትዮጵያ" የውይይት መድረክም ፋይዳ ለሀገር ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ ያለውን ጥቅም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
አዜአ የብሪክስ የሚዲያ ፕሬዚዲዬም አባል በመሆን ፋይዳ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊ ቀለም እንዲኖረው ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።