ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን በመዲናዋ በርካታ የህዝብ መዝናኛ ፓርኮችን ተረክቦ እያስተዳደረ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ጥር 29/2017 (ኢዜአ)፦

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2017(ኢዜአ) በመዲናዋ በርካታ የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች መገንባታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡

የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች ለህብረተሰቡ መዝናኛነት፣ ለቱሪስት መስህብነትና ለስራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ነጻነት ዳባ፤ ኮርፖሬሽኑ በመንግስትና በተለያዩ ተቋማት አማካኝነት የለሙ የህዝብ መዝናኛ ፓርኮችን ተርክቦ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ እየሰራ ይገኛል፡፡


 

የህዝብ መዝናኛ ፓርኮችን በመከታተል ለህብረተሰቡ ምቹ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግም የተለያዩ ስራዎች በመሥራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመዲናዋ የተገነቡና በመገንባት ላይ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች የህዝብ መዝናኛ ቦታዎችን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውንም የገለጹት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፤ ኮርፖቴሽኑ እስከ አሁን ተገንብተው የተጠናቀቁ በርካታ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን መረከቡን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የህዝብ መዝናኛ ፓርኮችን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ የማድረግ፣ የማልማትና ነባሮቹንም የማደስ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በዘርፉ የግሉን ሴክተር ለማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በግማሽ ዓመቱ በኮሪደር ልማት የተገነቡ የህዝብ መዝናኛዎችን ሳይጨምር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የህዝብ መዝናኛ ፓርኮችን መጎብኘታቸውንም ተናግረዋል።

በኮርፓሬሽኑ ስር የሚገኙ የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች አገልግሎት በአብዛኛው በነጻ መሆኑን የገለጹት ስራ አስፈጻሚዋ በውስን ፓርኮች ላይ ለተለያዩ አገልግሎቶች መሸፈኛ ሲባል አነስተኛ ገቢ እንደሚሰበሰብ ጠቅሰዋል፡፡

 በዚህም በግማሽ ዓመቱ 60 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉንና ከአምስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የስራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም