ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የጀመረውን የሪፎርም ስራ ይበልጥ ማጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የጀመረውን የሪፎርም ስራ ይበልጥ ማጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤ጥር 28/2017(ኢዜአ)፦ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የጀመረውን የሪፎርም ስራ ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የምስክ ምልከታ አድርጓል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በደምበኞች አገልግሎት በተለይም በጉዞ ሰነድ ዝግጅት፣ የፓስፖርት ዕድሳት፣ አዲስ ፓስፖርት እና የኢ- ፓስፖርት አሰጣጥ ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ተመልክተዋል።
የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ በመስክ ምልከታው በተቋሙ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ሰራዎች መመልከታቸውን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በማድረግና አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ እያከናወነ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ አገልግሎቱ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመሥጠት ፍጥነት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እና የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
አገልግሎቱ አሰራሮቹን ለማሻሻል ለሚያከናውናቸው ተግባራትም የቋሚ ኮሚቴው ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው አገልግሎቱ ከነበረበት ውስብስብ ችግር ለመላቀቅ የለውጥ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም ባከናወናቸው የለውጥ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ችግሮቹን በመቅረፍ የበለጠ ውጤታማ ለመሆንም የቴክኖሎጂ አሰራሮችን በመዘርጋት ተደራሽነቱን ለማስፋት የሚያስችሉ ተግባራትን በትኩረት እያከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህም በህገ ወጥ መልኩ ወደ ግለሰቦች ኪስ ይገባ የነበረውን ገንዘብ ወደ መንግስት ካዝና እንዲገባ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
ተገልጋዮች በበኩላችው አገልግሎቱ እየሰጠ ያለው አገልግሎት መሻሻሉን ገልጸው፤ በቀጣይ የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።