ቀጥታ፡

የሃላባ፣አንጋጫና ዋቶ የመንገድ ግንባታ ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በመለየት ፈጣን መፍትሔ ማበጀት ይገባል

አዲስ አበባ፤ጥር 28/2017(ኢዜአ)፦በሃላባ፣አንጋጫና ዋቶ የመንገድ ግንባታ ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በመፍታት ግንባታው በተቀመጠለት ጊዜ ሊጠናቀቅ እንደሚገባ የህዝበ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሃላባ፣ አንጋጫና ዋቶ የመንገድ ግንባታ አፈጻጸምን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የአስረጂ ውይይት አካሄዷል

ግንባታውን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በተቋራጭነት፣የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በባለቤትነትና የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በአማካሪነት በጋራ እንደሚያከናውኑት ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ዮናስ አያሌው የመንገድ ግንባታውን በሚመለከት ሪፖርት አቅርበዋል።

ኮርፖሬሽኑ የአሰራር ስርዓቱን በማሻሻል ዘርፉን ተወዳዳሪና ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን በማስታወስ በመንገድ፣ በቤትና በተለያዩ መሰረተ ልማቶች የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን አንስተዋል።

በሃላባ፣አንጋጫና ዋቶ የመንገድ ፕሮጀክት በአጋር አካላት መፈጸም ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በወቅቱ ባለመፈፀማቸው ፕሮጀክቱን በጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ አዳጋች እንደሆነባቸውም አስታውቀዋል።

በተለይም የወሰን ማስከበር ስራ በወቅቱ አለመከናወኑ ግንባታው እንዲጓተት ምክንያት መሆኑን ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር መልካ በቀለ ተቋሙ በሚያስገነባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች የወሰን ማስከበር ስራዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ የወሰን ማስከበር መረጃዎች የፍትሃዊነት ጥያቄን የሚያስነሱ በመሆናቸው የማጣራት ስራው ጊዜ እንደሚወስድ አክለዋል።

በዚህም በሃላባ፣አንጋጫና ዋቶ የመንገድ ግንባታ የሚከናወኑ የወሰን ማስከበር ስራዎችን በመመሪያው መሰረት ለመመለስ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው፥ በቀረበው ሪፖርት ላይ ጥያቄና አስተያየት ሰንዝረዋል።

ግንባታውን አስመልክቶ ቋሚ ኮሚቴው ተከታታይነት ያለው የመስክ ምልከታ እንዳደረገ አባላቱ ገልጸው እስካሁን ያለው የግንባታ አፈጻጸም በርካታ ጉድለቶች እንዳሉበት ዘርዝረዋል።

በቅርቡ በተደረገው ምልከታም ግንባታው 12 በመቶ ብቻ መፈጸሙን ገልጸው ይህም የአካባቢውን ነዋሪዎች ለእንግልት መዳረጉን የቋሚ ኮሚቴው አባላት አስታውቀዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ በባለድርሻዎች መካከል ያለውን ክፍተት በመፍታት ግንባታው በተቀመጠለት ጊዜ ሊጠናቀቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሃመድ አብዱ በግንባታው መጓተት የአካባቢው ማህበረሰብ ለተለያዩ ችግሮች መዳረጉን አንስተዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በምልከታው ወቅት ያነጋገራቸው ግለሰቦች ፕሮጀክቱ በወቅቱ ባለመጠናቀቁ ህክምናን ጨምሮ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለማግኘት አዳጋች እንደሆነባቸው መታዘቡን አስረድተዋል።

በተጨማሪም በአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ጫና በማሳደሩ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አክለዋል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽ በተቋራጩና በፕሮጀክቱ ባለቤት መካከል የሚታየውን ክፍተት በመለየት መፍትሔ ማመላከት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

የሃላባ፣ አንጋጫና ዋቶ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በጥር 2013 ዓ.ም ግንባታው በይፋ የተጀመረ ሲሆን በሶስት ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይደረጋል መባሉ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም