ቀጥታ፡

አየር መንገዱ የሀገር ውስጥ በረራ ደንበኞቹን በጊዜያዊነት በዓለም አቀፍ በረራ ማስተናገጃ እንዲጠቀሙ አሳሰበ

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ በረራ ደንበኞቹን በጊዜያዊነት በዓለም አቀፍ በረራ ማስተናገጃ እንዲጠቀሙ አሳስቧል።

አየር መንገዱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ ዛሬ ከቀኑ 6:30 በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሀገር ውስጥ መንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ ውስጥ ወደ በረራ ይዞ መግባት ከሚከለከሉ ቁሳቁሶች መካከል ከመንገደኞች የሚሰበሰብ የሲጋራ መለኮሻ (ላይተር) ጊዜያዊ የማስቀመጫ ስፍራ ውስጥ ጭስ በመከሰቱ ለመንገደኞች ደህንነት ሲባል ሕንፃው ለጊዜው አገልግሎት አቋርጧል ብሏል፡፡

በመሆኑም በዛሬው ዕለት ወደ ሀገር ውስጥ መዳረሻዎች የሚጓዙ መንገደኞች በዓለም አቀፍ መንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል በኩል ወደ በረራቸው እንዲሳፈሩ አሳስቧል፡፡

ለተፈጠረው መጉላላት መንገደኞችን ይቅርታ የጠየቀው አየር መንገዱ፤ ከነገ ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለመደው የሀገር ውስጥ ተርሚናል አገልግሎት መስጠት እንደሚቀጥልም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም