ቀጥታ፡

ሐይቆችን ከእምቦጭ አረም የመታደግ ጥረቱ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

በኢትዮጵያ አይነተ ብዙ መጤ የዕጽዋት ዝርያዎች በውሃ አካላት፣ በእርሻና በግጦሽ መሬት ላይ በፍጥነት እየተዛመቱ መልከ ብዙ አደጋ እያስከተሉ ነው።

በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መጤ አረሞች በውሃማ አካላት ላይ እየተስፋፉ በመምጣታቸው በብዝሐ ሕይወት ላይ የሕልውና ስጋት ደቅነዋል።

በግዙፉ የጣና ሐይቅ ጨምሮ በውሃማ አካላት ብዝሐ ሕይወት አደጋ ከደቀኑ መጤ አረሞች መካከል እምቦጭ ትልቁን ድርሻ ይዟል።

እምቦጭ የውሃ መጠን በመቀነስ፣ የዕጽዋትና የእንስሳት ብዝሃ ሕይወት በማመናመን ካለው ከፍተኛ ስጋት አኳያ ባለፉት ዓመታት ስጋቱን ለመቀልበስ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጥረት አድርገዋል።

ክልሎች በየውሃማ አካላቱ እየተስፋፋ የመጣውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል በሰው ጉልበት እና በሜካኒካል መንገዶች ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል።

ኢዜአ እምቦጭን ጨምሮ በፍጥነት እየተዛመቱ የሚገኙ የብዝሐ ሕይወት አደጋ የሆኑ የደቀኑ አረሞችን ለመከላከል ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች ምን ላይ እንዳሉ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎችን አነጋግሯል።


 

በአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አወቀ ይታይ፤ በክልሉ ጣና ሃይቅን የወረረውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ በዘመቻ መልክ ሲሰሩ የነበሩ ስራዎች አስታውሰዋል።

የጣና ሐይቅ የእምቦጭ አረም በዘላቂነት ለመፍታት የክልሉ መንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚሻ ገልጸዋል።

ከዚህ በፈት የእምቦጭ ጉዳይ አጀንዳ በማድረግ ችግሩን ለመቀልበስ ጥሩ እንቅስቃሴ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን በወቅታዊ ሁኔታዎች ሳቢያ መቀዛቀዝ እንዳለ አንስተዋል።

በዚህም የእምቦጭን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ ዳግም በማነቃነቅ አሁናዊ መቀዛቁዙን ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።


 

በኦሮሚያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የብዝሃ ሕይወት ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር ብርሃኑ ኢደቲ እንዳሉት ደግሞ በክልሉ የተከሰቱ መጤ አረሞችን ለመከላከልና መቆጣጠር በልዩ ትኩረት ሲሰራ ቆይቷል።

እምቦጭን ጨምሮ መጤ አረሞችን ለለመቀነስ ህብረተሰቡ፣ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በትብብር መስራታቸውን ገልፀዋል።

በዚህም በባቱ ደንበል ሐይቅ ላይ ተከስቶ የነበረውን የእምቦጭ አረም መቀነስ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ይሁንና አሁንም ቢሆን ከችግሩ ስፋት አኳያ ተቋማዊ የሆነ ተከታታይነት ያለው ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መለሰ ማርዮ(ዶ/ር) እምቦጭና ሌሎች መጤ የዕጽዋት ዝርያዎችን የመከላከል ጥረት የአንድ ሰሞን ዘመቻ መሆን እንደሌለበት ያምናሉ።

አረሞቹ ማጥፋት አዳጋች እንደሆነ የገለጹት ዶክተር መለሰ፤ አሉታዊ ተጽዕኖውን ግን መቀነስና መቆጣጠር እንደሚቻል ተናግረዋል።

በመሆኑም በአካባቢና ብዝሃ ሕይወት ላይ ከሚያስከትሉት ከፍተኛ ጉዳት አኳያ አረሞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እና የጋራ አደረጃጀት መፍጠር እንደሚገባ ነው ያነሱት።

ይህ ደግሞ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም የሚጠቅይቅ በመሆኑ ከተለያዩ ምንጮች ፋይናንስ በማፈላለግ እንዲሁም የህብረተሰቡን አቅም በመጠቀም የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም