ፓርኩን ከእሳትና ሌሎች ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለመከላከል የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ፓርኩን ከእሳትና ሌሎች ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለመከላከል የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሮቤ፤ ጥር 28/2017(ኢዜአ)፡- የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ከእሳትና ሌሎች ሰው ሰራሽ አደጋዎች መከላከል የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የፓርኩ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሻሚል ከድር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ፓርኩን ከእሳትና ሌሎች ሰው ሰራሽ አደጋዎች መከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በፓርኩ ላይ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ሰው ሰራሽ አደጋዎች መካከል ሰደድ እሳት፣ ህገ-ወጥ ሰፈራና ልቅ ግጦሾ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይ የበጋው ሞቃታማ አየር ለእሳት አደጋ መቀስቀስ ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር ህብረተሰቡንና አጋር አካላትን በማሳተፍ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በፓርኩ ክልል ባለፉት አራት ዓመታት የእሳት አደጋ አለመከሰቱን የጠቆሙት ኃላፊው በአሁኑ ወቅትም ህብረተሰቡን ያሳተፈ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ የፓርኩ አዋሳኝ በሆኑ ዲንሾ፣ ጎባ፣ አዳባና ሌሎች አዋሳኝ ወረዳዎች ውስጥ በየደረጃው ካሉ አመራር አባላትና የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር የአደጋ ቅድመ መከላከል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቻውን አስረድተዋል።
እንዲሁም የእሳት አደጋ ስጋት ናቸው ተብለው በጥናት በተለዩ የፓርኩ የተለያዩ ቦታዎችም በእሳት አደጋ መከላከል ሙያ የሰለጠኑ 192 አባላት ያላቸው 16 የእሳት አደጋ ተከላካይ ብርጌድ መቋቋማቸውን ተናግረዋል።
ለብርጌድ አባላቱ አልባሳት፣ ትጥቅና የእሳት ማጥፊያ መሳሪያዎች ማሟለት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች በመመቻቸት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ለእሳት አደጋ ቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት በየደረጃው ከሚገኙ የመስተዳድር አካላትና በጎ አድራጊ ድርጅቶች በበጀትና በስልጠና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
ፓርኩ በዓለም ቅርስነት ሲመዘገብ ሊሟሉ የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረገ መሆኑን በመገንዘብ ፓርኩን ከአደጋ ስጋት ነፃ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው አቶ ሻሚል የተናገሩት።
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከ2 ሺህ ስኩዌሬ ካሬ ሜትር በላይ መሬት የሚያካልል ሲሆን በውስጡም የደጋ አጋዘን፣ ጦጣ፣ ፍልፈልን ጨምሮ ሌሎች አያሌ የዕጽዋትና አዕዋፍ መገኛ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም(ዩኔስኮ) በ45ኛው የአለም የቅርስ ጉባኤ ላይ ፓርኩን በቋሚ ቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል።