ቀጥታ፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስፖርት ውድድር የስፖርት ዓይነቶችና የተሳታፊ ስፖርተኞችን ቁጥር በማሳደግ ተጠናክሮ ይቀጥል - ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2017(ኢዜአ)፡- የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስፖርት ውድድር የስፖርት ዓይነቶችና የተሳታፊ ስፖርተኞችን ቁጥር በማሳደግ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሲካሄድ የቆየው የስፖርት ፌስቲቫል በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቋል።


 

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ኮራ ጡሹኔ በውድድሩ መዝጊያ ላይ እንደገለጹት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስፖርት ውድድር ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተጠናክሮ የሚካሄድ ይሆናል።


 

ሚኒስቴሩ ተሳታፊ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በስፖርት አይነቶችና የተሳታፊ ስፖርተኞችን ቁጥር በማሳደግ የበለጠ ደማቅና ቀጣይነት ያለው አመታዊ ክንውን ለማድረግ ሰፊ እቅድ መያዙንም ገልጸዋል፡፡

የስፖርት ፌስቲቫሉ በተሳታፊ ተቋማትና ተማሪዎች እንዲሁም ለዜጎች አንድነት፣ እድገትና ልማት አስተዋጽኦ በሚያደርግ መልኩ እንደሚቀረጽም መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የውድድሩ አስተናጋጅ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳው(ዶ/ር) በበኩላቸው በእግር ኳስ፣ በቴኳንዶ፣ በአትሌቲክስ፣ በቼዝና በባህላዊ ስፖርቶች የተካሄደው ፌስቲቫል በከፍተኛ ተሳትፎና በስፖርታዊ ጨዋነት መጠናቀቁን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አባይ በላይሁን በበኩላቸው ውድድሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችል በመሆኑ የዘርፉ ባለድርሻዎች በትኩረት ሊሰሩበት ይገባል ብለዋል።


 

በውድድሩ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን በወንዶች እግር ኳስ ወሎ፣ በሴቶች አትሌቲክስ መከላከያ፣ በወንዶች አትሌቲክስና በአጠቃላይ አትሌቲክስ ሐረማያ፣ በወርልድ ቴኳንዶ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲዎች አሸናፊዎች ሲሆኑ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የምስጉን ዋንጫ ተሸላሚ መሆኑም ተመላክቷል።

የውድድሩ አሸናፊዎች ከትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጠሹኔና እና ከሌሎች እንግዶች እጅ ዋንጫ መቀበላቸውም በመረጃው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም