በመዲናዋ የህዝብ ንጽህና ቤት ፍላጎትን ለማሟላት ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የህዝብ ንጽህና ቤት ፍላጎትን ለማሟላት ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የህዝብ ንጽህና ቤት ፍላጎትን ለማሟላት ባለድርሻ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት እንደሚገባቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቱዩት ከከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር በመዲናዋ የተገነቡ የህዝብና የጋራ ንጽህና ቤቶችን ሽፋንና ስታንዳርድ ለማወቅ ያስጠናውን ጥናት ግኝት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ በካፒታል ሆቴል ይፋ አድርጓል።
በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቱዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ተካልኝ አርፊቾ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፣ በአዲስ አበባ አስራ አንድ ክፍለ ከተሞችን በተደረገው ጥናት የንጽህና ቤቶች ሽፋን ከመዲናዋ ፍላጎትና ተደራሽነት፣ ከዲዛይንና ከጥራት አኳያም ጥያቄ የሚነሳባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
ንጽህና ቤቶቹ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን ያላሟሉ፣ በቂ ውሃና ሳሙና የሌላቸው እንዲሁም ህጻናትንና አካል ጉዳተኞችን ግምት ውስጥ ያስገቡ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
ከፍተኛ ተመራማሪው የከተማዋን የንጽህና ቤት ፍላጎቱንና አቅርቦቱ ለማመጣጠን ተጨማሪ 357 የንጽህና ቤቶችን መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ይህን ለማሟላት ተቋማት ተቀናጅተውና ተናበው መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቱዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቃዱ ጸጋ በበኩላቸው፤ ባለፉት ወራት ኢንስቲቱዩቱ የአዲስ አበባ ከተማ የመጸዳጃ ቤት ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ ሃሳቦችን ለማመላከት ጥናት ሲያድርግ መቆየቱን አመላክተዋል።
በዚህም የተገኙ ግኝቶችም ለከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ማቅረብ መቻሉን ጠቁመው፤ በቀጣይም አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ ኢንስቲቱየቱ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ አበባን ውብና ጽዱ ለማድረግ በአሁኑ ወቅት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ሃላፊ ግርማ ሰይፉ ናቸው፡፡
በንጽህና ቤቶች በኩል የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከቀረበው ጥናት በርካታ ግብዓት ማግኘት ችለናል ያሉት አቶ ግርማ፤ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሸቲቭ እና በኮሪደር ልማቱ በርካታ የንጽህና ቤቶች መገንባታቸውን ይታወቃል፡፡
በዚህም በከተማዋ የነበረውን ከፍተኛ የንጽህና ቤት አቅርቦት ችግር በተወሰነ ደረጃ መፍታት ተችሏል፡፡