ኢትዮጵያ በሚዲያ ዘርፍ ጭምር የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን የጀመረችውን ሥራ በጋራ መደገፍ ይገባል - የኬንያ ዩናይትድ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ዋና ዳይሬክተር ኒኮዲሞስ ቦሬ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሚዲያ ዘርፍ ጭምር የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን የጀመረችውን ሥራ በጋራ መደገፍ ይገባል - የኬንያ ዩናይትድ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ዋና ዳይሬክተር ኒኮዲሞስ ቦሬ
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሚዲያ ዘርፍ ጭምር የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን የጀመረችውን ሥራ በጋራ መደገፍ ይገባል ሲሉ የኬንያ ዩናይትድ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ዋና ዳይሬክተር ኒኮዲሞስ ቦሬ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር አፍሪካ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ የምትሳልበት አግባብ አሉታዊ እንደሆነ አንስተው፤ የአፍሪካን ገጽታ የሚገነባ አፍሪካዊ ሚዲያ ማቋቋም እንደሚገባ መናገራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት በዲጂታል አማራጭ ፓን አፍሪካዊ ሚዲያ ለመገንባት እየሰራ ይገኛል።
በኬንያ ዩናይትድ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ዋና ዳይሬክተር ኒኮዲሞስ ቦሬ የተመራ ልዑክ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጎብኝቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በሚዲያው ዘርፍ እያሳየ ያለው አስተዋጽኦና እድገት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
ተቋሙ ራዕዩን ለማሳካት የሚያግዝ ዘመናዊ የሚዲያ ቴክኖሎጂ መታጠቁንና ሙያዊ ክህሎት የተላበሰ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል አደረጃጀት መኖሩን መገንዘባቸውንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሚሰራቸው ሥራዎች የኢትዮጵያ መንግሥት በሚዲያ ዘርፍ ጭምር የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን የጀመረውን ሥራ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
አፍሪካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ለዓለም ማቅረብ የሚቻለው ኢትዮጵያ በሚዲያው ዘርፍ የጀመረችውን ሥራ መደገፍ ሲቻል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ መገለጫ ጦርነትና ድርቅ አይደለም፤ ይልቁንም ትልቅ ጸጋና ኃብትም ጭምር ነው ያሉት የኬንያ ዩናይትድ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ዋና ዳይሬክተር ኒኮዲሞስ ቦሬ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ይዛው የተነሳችውን ኃሳብ ሁሉም ሊደግፈው ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የመረጃ የልብ ምት ለመሆን እያደረገች ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያና ኬንያ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ጠቅሰው ይህ ግንኙነት ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ኬንያ ወዳጆች ብቻ አይደሉም፤ ድንበር ዘለል ግንኙነት ያላቸው የተዋለዱና የተሳሰሩ ሕዝቦችም ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም ግንኙነታቸውን የበለጠ በማጠናከር ለጋራ ዓላማና ለአፍሪካዊ እሳቤዎች መጎልበት በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።
በኬንያ ዩናይትድ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ዋና ዳይሬክተር ኒኮዲሞስ ቦሬ የተመራ ልዑክ በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ በተካሄደው ሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ላይ መታደሙ ይታወቃል።