ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድምጽ የሚሆን ሚዲያ ለመገንባት የጀመረችው ሥራ የአህጉሪቱን ጥቅሞች በጋራ ለማስጠበቅ ያግዛል - ፒተር ላም ቦዝ

አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድምጽ የሚሆን ሚዲያ ለመገንባት የጀመረችው ሥራ የአህጉሪቱን ጥቅሞች በጋራ ለማስጠበቅ እንደሚያግዝ የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ንቅናቄ(SPLM) ዋና ጸሃፊ ፒተር ላም ቦዝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በ35ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ የአፍሪካ ድምጽ የሚሰማበት፣ የፓን አፍሪካዊነት ድምጽ የሚንጸባረቅበት የጋራ አህጉራዊ ሚዲያ ሊኖረን ይገባል ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።


 

ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ በሚዲያ ዘርፍ የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን እየሰራች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ይህን ታሳቢ በማድረግ በዲጂታል አማራጭ የአፍሪካን ጥቅሞች ለማስጠበቅ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል።

በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጉባኤ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የተገኙት የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ንቅናቄ(SPLM) ዋና ጸኃፊ ፒተር ላም ቦዝ፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አዲሱን የሚዲያ ኮምፕሌክስና የዲጂታል ሚዲያ መሰረተ ልማትን ጎብኝተዋል።

ዋና ጸኃፊው ፒተር ላም ቦዝ በዚሁ ጊዜ የአፍሪካን አቅሞች ለማስተሳሰርና የጋራ ትርክት ለመፍጠር ጠንካራ አፍሪካዊ ሚዲያ ሊኖር እንደሚገባም ተናግረዋል።


 

ከዚህ አኳያ ኢዜአ በዲጂታል አማራጭ የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን “pulse of Africa’’ በሚል ሥያሜ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ተደራሽ ለመሆን የጀመራቸው ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ይህም አህጉሪቱ በልማትና በሌሎች መስኮች ያላትን እምቅ አቅም ለማስተዋወቅ ሁነኛ መፍትሄ ይሆናል ብለዋል።

ከአፍሪካ ውጭ ያሉ መገናኛ ብዙኃን የአፍሪካውያንን እውነት በማስተዋወቅ ረገድ ውስንነት እንዳለባቸው በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድምጽ የሚሆን ሚዲያ ለመገንባት የጀመረችው ሥራ የአህጉሪቱን ጥቅሞች በጋራ ለማስጠበቅ ያግዛል ነው ያሉት።

ዋና ጸኃፊው ፒተር ላም ቦዝ፤ በአፍሪካ በሚዲያው ዘርፍ የሚታየውን ውስንነት ለማስተካከል ኢትዮጵያ ወደ ፊት እየመጣች መሆኑን ኢዜአን በጎበኙበት ወቅት መታዘባቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሚዲያዎች ከኢዜአ ጋር በመረጃ ልውውጥ መተሳሰር እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም