በአፍሪካ ጠንካራ የእንስሳት ጤና ስርዓትን ለመገንባት አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ጠንካራ የእንስሳት ጤና ስርዓትን ለመገንባት አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2017(ኢዜአ)፡- በአፍሪካ ጠንካራ የእንስሳት ጤና ስርዓትን በመገንባት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
26ኛው የዓለም እንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፤ የእንስሳት ሀብቷ ለግብርና ጥቅል ምርት የ40 በመቶ እንዲሁም ለጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት የ20 በመቶ አስተዋፅኦ አለው።
በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ አፍሪካ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ቢኖራትም የምግብ ዋስትናን አላረጋገጠችም ብለዋል።
ኢትዮጵያም አብዛኛው ህዝቧ በግብርና የሚተዳደር እና በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ ሳትሆን መቆየቷን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ለግብርና ዘርፍ በተለይም ለእንስሳት ሀብት ልማት፣ ለምግብ ዋስትና እና ደህንነት መሻሻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ እመርታዊ ለውጥ በማስመዝገብ የምግብና ስርዓተ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ገቢራዊ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የስጋና ወተት፣ የዶሮና እንቁላል፣ የማር እና የዓሳ ምርታማነትን በማሳደግ የተትረፈረፈ የምግብ ምርትና የተመጣጠነ የምግብ ስርዓትን ማምጣትን ያለመ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
መንግሥት መርሀ ግብሩ ግቡን እንዲመታ ለእንስሳት ጤና ትኩረት መስጠቱን ገልጸው፤ የእንስሳት ህክምና አገልግሎትን የማስፋፋትና የማዘመን ሥራ እንዲጠናከር መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ ብቻዋን ልታሳካው የምትችለው ግብ ባለመኖሩ የድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታን፣ የአየር ንብረት ለውጥን ተፅዕኖ ለመቋቋም አህጉራዊ ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል።
የእንስሳት በሽታ ቁጥጥርና የመከላከል አቅምን ለማሳደግ የሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በቅንጅት መስራት እና በመርህ መመራት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም በትብብር፣ ፈጠራ እና በጋራ ሃላፊነት መሥራት እንደሚገባ አሳስበው፥ ኢትዮጵያ ለእንስሳት ጤና እና ደህንነት ዓለም አቀፋዊ ግቦች እንዲሳኩ የበኩሏን እንደምትወጣም ገልጸዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ፥ የእንስሳት ሀብት የአፍሪካ አጀንዳ 2063ን ለማሳካት፣ የምግብ ስርዓትን እና ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሻሻል ወሳኝ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያም የእንስሳት ሀብት በቤተሰብ ደረጃ እንዲሁም ለሀገር ኢኮኖሚ ያላቸው ሚና ገዙፍ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በግብርና በተለይም በእንስሳት ሀብት ኑሮውን እንደሚመራ አንስተዋል።
የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ጉባኤ ልዑክ ፕሬዝዳንት ሱዛና ፖምቦ በበኩላቸው፥ አፍሪካ የብዝኃ ህይወት ሀብትን የታደለች ብትሆንም የእንስሳት ጤና ስጋት የተደቀነባትና የንግድ ስርዓት ደካማነት እንደሚስተዋልባት ጠቅሰዋል።
ጉባኤው በአፍሪካ የእንስሳት ህክምና ላይ ያሉ ዕድሎችናና ስጋቶችን በመተንተን የመፍትሔ እርምጃዎችን ለማጠናከር እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ለተጽዕኖ የማይበገር እና ዘመኑን የዋጀ ተክኖሎጂን ያሟላ ዘመናዊ የእንስሳት ህክምና አገልግሎትን በመገንባት የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ አንስተዋል።
የአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ አካባቢ ኮሚሽን የኮሚሽነሩ ተወካይ ሃያን ሳሊህ(ዶ/ር)፥ በፍጥነት እያደገ ከሚገኘው የህዝብ ቁጥሯ አንጻር ዕድልና ስጋት ከፊቷ ተደቅነዋል ብለዋል።
ከፍተኛ የምግብ ፍላጎት፣ የእንስሳት በሽታ መስፋፋት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እና የንግድ ስርዓት ደካማ መሆን ስጋት ናቸው ብለዋል።
በሌላ በኩል የእንስሳት ሀብትን ለመጠቀም የተጀመሩ ኢኒሼቲቮች፣ የህክምና አገልግሎቶች መስፋፋት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ትልቀ ተስፋ መሆናቸውን አንስተዋል።
የአፍሪካ መሪዎች በዚህ ወር መጀመሪያ በኡጋንዳ ካምፓላ ባካሄዱት አስችኳይ ጉባኤ ችግርን መቋቋም የሚችልና ዘላቂ የምግብ ስርዓት መገንባትን ዓላማ ያደረገ የቃል ኪዳን ስምምነትን ማጽደቃቸውም ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የቃል ኪዳን ስምምነቱ የአጀንዳ 2063 አካል የሆነው የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም ካዳፕ (CAADAP) ትግበራን ከዳር ለማድረስ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
ካዳፕ በፈረንጆቹ 2035 የድህረ ምርት ብክነትን በ50 በመቶ ለመቀነስ፤ የግብርና ምግብ ውጤቶችን በመቶ ለማሳደግ እንዲሁም በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የግብርና ምግብ ምርቶች የንግድ ልውውጥ በሶስት እጥፍ ለማሳደግ ግብ አስቀምጧል።
ይህን ለማሳካት የእንስሳት ሀብት ልማትን ማጠናከር ወሳኝ ነው ያሉት ተወካዩ፥ ሆኖም ድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት በሽታ ስጋት ደቅኗል ብለዋል።
ከእነዚህም መካከል በበግና ፍየል ላይ የሚከሰተው የደስታ በሽታ (Peste des Petits Ruminants (PPR) አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፥ ዝቅተኛ አቅም ያላቸው አርሶ አደሮች ላይ የሚያስከትለው ጫና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
በሽታውን ማስወገድ ከእንስሳት ጤና ያለፈ ለትውልድ የማሰብ ሞራላዊ ግዴታና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የላቀ መሆኑን ጠቅሰው፥ የአፍሪካ ህብረት ራሱን የቻለ ተቋም አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አንስተዋል።