ለስፖርት ዘርፉ ማንሰራራት በተተኪ ስፖርተኞች ትኩረት ይደረጋል- ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
ለስፖርት ዘርፉ ማንሰራራት በተተኪ ስፖርተኞች ትኩረት ይደረጋል- ሚኒስቴሩ
ሶዶ፤ ጥር 27/2017 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ስፖርት ዘርፍ እንዲያንሰራራ በተተኪ ስፖርተኞችን ልማት ላይ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
"የታዳጊ ስፖርተኞች ልማት ለአሸናፊ ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የስፖርት ዐውደ ጥናት በሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዩ መሀመድ ፤ ከለውጡ ወዲህ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት መንግስት ለስፖርቱ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በአገሪቱ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ለስፖርቱ ዕድገትና እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ስፖርት እንዲያንሠራራ በታዳጊዎች ላይ መሥራት ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ትኩረት በመስጠት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ከህግና አሠራር እንዲሁም ከአገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ውድድር ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፋንታዬ ገዛኸኝ በበኩላቸው፤ በአገራችን ጤናማ ስፖርትን ለማበልፀግ አበረታች ቅመሞችን መከላከል ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የፌደራልና የክልል የዘርፉ አመራር አባላትና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።