ቀጥታ፡

የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማጎልበት የሚያግዝ የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማጎልበት የሚያግዝ የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ ይፋ ተደረገ።

በግብርና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና ጌትስ ፋውንዴሽን በጋራ የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታው በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2025 እስከ 2032 የሚተገበረው ነው።

ፍኖተ ካርታው የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንዳሉት የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ ዘርፉን ለማዘመን እና ገበያ ተኮር እንዲሆን ለማስቻል ያግዛል።

የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን በስማርት ስልኮች ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የግብርናው መረጃዎችን በአንድ ቋት ለመያዝና ለማዘመን፣ የግብርና ግብዓትን ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ብድርና ኢንሹራንስን ጨምሮ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ከምርት እስከ ገበያ ባለው የእሴት ሰንሰለት የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት በማጎልበት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚያግዝም እንዲሁ።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ከሚሰራባቸው ዘርፎች መካከል የዲጂታል ግብርና አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዘርፉን በማዘመን ይገጥሙ የነበሩ ተግዳሮቶች ለመፍታት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል።

ዲጂታል ግብርና በትክክለኛ የመረጃ ትንተና ላይ የተመሰረተ ፈጣን ውሳኔ በመስጠት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም