የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ከእሳት አደጋ ሥጋት ለመጠበቅ የጥንቃቄ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ከእሳት አደጋ ሥጋት ለመጠበቅ የጥንቃቄ ስራዎች እየተከናወኑ ነው
ጎንደር፤ ጥር 27/2017 (ኢዜአ)፦የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ከእሳት አደጋ ሥጋት ነጻ ለማድረግ የሚያስችሉ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የፓርኩ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማሩ ቢያድግልኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የበጋው ሞቃታማ አየር ለእሳት አደጋ መቀስቀስ ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር ህብረተሰቡንና አጋር አካላትን በማሳተፍ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።
የፓርኩ አዋሳኝ በሆኑት ደባርቅ፣ ጃናሞራ፣ በየዳ እና አዲአርቃይ ወረዳዎችም ከህብረተሰቡ ለተመለመሉ 120 ነዋሪዎች የእሳት አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ስልጠናና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በፓርኩ ክልል በህገ ወጥ መንገድ የሚከናወን የማር ቆረጣ ሥራ ለእሳት አደጋ መከሰት ዋነኛ ምክንያት በመሆኑ ህብረተሰቡን በባለቤትነት ያሳተፈ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የእሳት አደጋ ስጋት ናቸው ተብለው በጥናት በተለዩ የፓርኩ የተለያዩ ቦታዎችም በእሳት አደጋ መከላከል ሙያ የሰለጠኑ 40 የእሳት አደጋ ተከላካይ ብርጌድ አባላት ስምሪት መደረጉን ተናግረዋል።
ለብርጌድ አባላቱ አልባሳት፣ ትጥቅና የእሳት ማጥፊያ መሳሪያዎች መሟላታቸውንም ጠቁመዋል።
በፓርኩ ክልል ባለፉት ዓመታት ተከስቶ በነበረ የእሳት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው የተፈጥሮ ደኖችና የጓሳ ሣርም በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መልሰው ማገገማቸውን አስረድተዋል።
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ተመዘገበ
የፓርኩ ስነ ምህዳርና ብዝሃ ሕይወትን መጠበቅ እንዲቻል በየዓመቱ በተከናወነው የችግኝ ተከላ ሥራም የፓርኩን የተፈጥሮ ሚዛን በመጠበቅ ለዱር እንስሳቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አመልክተዋል።
ለእሳት አደጋ ቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት የመስተዳድር አካላትና ዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅቶች በበጀትና በስልጠና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም አቶ ማሩ አመልክተዋል።
የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በውስጡም ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት መገኛ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል።