ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ የጋራ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ሊያቋቁሙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ የጋራ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ሊያቋቁሙ ነው
አዲስ አበባ፤ጥር 27/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችላቸው የጋራ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ለማቋቋም ከስምምነት ላይ ደረሱ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከቼክ ሪፐብሊክ የኢንደስትሪና ንግድ ምክትል ሚኒስትር ጄ ካቫሊሬክ ጋር ተወያይተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ትናንት በኘራግ በተካሄደው የኢትዮ-ቼክ ሪፐብሊክ የፖለቲካ ምክክር ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል።
ሚኒስትር ዴኤታ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከቼክ ሪፐብሊክ የኢንዱስትሪና ንግድ ምክትል ሚኒስትር ጄ ካቫሊሬክን ጨምሮ ከተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ የሁለቱን አገራት ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በውኃ እና ኢነርጂ ፣ በማምረቻ ዘርፍ እንዲሁም በመከላከያ ኢንዱስትሪ ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
አምባሳደሩ ከቼክ ሪፐብሊክ የኢንደስትሪና ንግድ ምክትል ሚኒስትር ጄ ካቫሊሬክ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።
በውይይቱም የሁለትዮሽ ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከር የተዘጋጀውን የጋራ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ምስረታ ረቂቅ ሠነድ በአጭር ጊዜ ተፈራርመው ወደ ሥራ ለማስገባት ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በርካታ የቼክ ሪፐብሊክ ባለሀብቶች የተገኙበት የኢትዮጵያ የቢዝነስ ፎረም ትናንት በፕራግ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።