በፕሪሚየር ሊጉ የሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ የሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬም ቀጥሎ ሲውል ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
መቀሌ 70 እንደርታ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች መካከል በሶስቱ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ግቦችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ22 ነጥብ 9ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ ካለፉት አምስቱ የሊጉ ጨዋታዎች በአንዱ ድል ሲቀናው ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ አራት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ስድስት ግቦች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ20 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል።
የዕለቱ ሁለተኛ መርሃ ግብር አርባምንጭ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕናን ምሽት 12 ሰዓት ላይ ያገናኛል።
አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ውስጥ ሶስት ጊዜ ሲያሽንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ቡድኑ በጨዋታዎቹ ላይ ሰባት ጎሎችን ከመረብ ሲያገናኝ አራት ግቦች ተቆጥረውበታል። በሊጉ 23 ነጥብ በመሰብሰብ 7ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሀዲያ ሆሳዕና በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሽንፈት አጋጥሞታል። በቀሪው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል።
ቡድኑ በአምስቱ ጨዋታዎች አምስት ጎሎችን አስቆጥሮ በተመሳሳይ ሶስት ግቦችን በማስተናገድ በ26 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ18ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን መርሃ ግብሮች ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዳማ ከተማን 3 ለ 0 ሲረታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ድሬዳዋ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።