ኢትዮጵያ ከፍልሰት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ህግ አውጥታና የትብብር አደረጃጀቶችን ፈጥራ እየሰራች ነው - የፍትህ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከፍልሰት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ህግ አውጥታና የትብብር አደረጃጀቶችን ፈጥራ እየሰራች ነው - የፍትህ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከፍልሰት አስተዳደር ጋር በተያያዘ በርካታ አለም አቀፍ ስምምነቶችን መቀበሏንና ተግባራትን ለማከናወን ህግ አውጥታ እና የትብብር አደረጃጀቶችን ፈጥራ እየሰራች መሆኑን የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ገልጸዋል፡፡
አቶ በላይሁን ይርጋ ከኔዘርላንድስ የፍልሰት ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ፒተር ሹርማን ጋር በፍልሰት አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም አቶ በላይሁን ይርጋ በኢትዮጵያ ያለውን መደበኛ እና መደበኛ ያልሆነ የፍልሰት አስተዳደር ሁኔታን በተመለከተ ለልዩ መልዕክተኛው አብራርተዋል።
በዚህም ከፍልሰት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በርካታ አለም አቀፍ ስምምነቶችን መቀበሏንና ተግባራትን ለማከናወንም ህግ አውጥታ እና የትብብር አደረጃጀቶችን ፈጥራ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም መደበኛ ያልሆነው ፍልሰት በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖ አብራርተው ኢትዮጵያ የስደተኞች ተቀባይ ሀገር መሆኗንና በአሁኑ ወቅትም ከ26 ሀገራት ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
እነዚህን ተግባራት ለማከናወን የአጋር አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንና ከእነዚህ አጋር ሀገራት መካከልም የኔዘርላንድስ መንግስት አንዱ መሆኑን ማንሳታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።
እስካሁን ባለው ሂደት የኔዘርላንድስ መንግስት የኢትዮጵያ የፍልሰት አስተዳደር መደበኛ እንዲሆን፣ ወንጀሎቹን የመከላከልና የመቆጣጠር አቅም እንዲጠናከር እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል።
እንዲሁም compass የተሰኘው ፕሮጀክት ከስደት ተመላሾችን መልሶ ማቋቋም፣ የተጎጂዎች ጥበቃ አቅምን ለማጠናከር ማገዙን ገልፀው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም ቀደም ሲል የፍትህ ሚኒስቴር የግንዛቤ ፈጠራ ንቅናቄዎችን ለማድረግ፣ የብሄራዊ የቅብብሎሽ ስርዓት እንዲዘረጋና የተጠናከረ እንዲሆን ከማድረግ አንጻርም የነበረውን አስተዋጽኦ አንስተዋል።
በፍልሰት ፖሊሲ ዝግጅት እና በተለይም ለፍልሰት መነሻ የሚባሉ ጉዳዮችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የኔዘርላንድስ መንግስት ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም የሀገሪቱ ዋና ዋና የፍልሰት ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ በተለይም ወንጀሎቹን የመከላከልና የመቆጣጠር ዋና አጀንዳዎችን በዝርዝር ለልዩ መልዕክተኛው ማብራራታቸውም በመረጃው ተመላክቷል።
በዘርፉ ላይ ለሚከናወኑ መሰል ተግባራት ውጤታማነት የኔዘርላንድስ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አቶ በላይሁን መጠየቃቸው ተገልጿል፡፡
የኔዘርላንድስ መንግስት የፍልሰት ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ፒተር ሹርማን በበኩላቸው ፍልሰት በሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ደረጃ እያሳደረ ያለው ችግር እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በፍልሰት አስተዳደር ዙሪያ እየሰራቻቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ መሆኑንና የኔዘርላንድስ መንግስትም የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል፡፡